አሞኒየም ናይትሬት ፡ ቤይሩት ውስጥ የፈነዳው አደገኛ ኬሚካል በየትኞቹ አገሮች ተደብቆ ይገኛል?

የሊባኖሷን ዋና ከተማ ቤይሩትን ያየ በኬሚካል አይጫወትም።

ይሄ አሞኒየም ናይትሬት ኬሚካል ከቤይሩት ፍንዳታ በኋላ ሚዲያው ሁሉ ስሙን እያነሳ ያወሳዋል።

በስፋት ለግብርና ማዳበሪያነት ነው የሚውለው። ከዚያ ሌላ ማዕድን በማውጣት ሂደት ውስጥ ፍንዳታን ለመፍጠር አገልግሎት ላይ ይውላል።

አልፎ አልፎ ደግሞ መሬት ላይ ለሚጠመድ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች መስሪያነት ያገለግላል።

አሁን ስለ አሞኒየም ናይትሬት ሁሉም አገር መጨነቅ ጀምሯል። ደብቆ ያስቀመጠም መጋዘኑን እየወለወለ ነው። ኋላ የሚሆነው አይታወቅም!

ይህ ኬሚካል ምን ዓይነት ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል፣ ለምን ያህል ጊዜ፣ ጥንቃቄውስ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ጥብቅ መመሪያዎች አሉ።

ሐቁ ይህ ነው፤ ብዙ አገሮች ይህ አሞኒየም ናይትሬት ኬሚካል እንዳላቸው መናገር አይፈልጉም። ምክንያቱም ፈንጂ እያመረቱ እንደሆነ እንዳይጠረጠሩ ስለሚሰጉ ነው።

የሚከተሉት አገራት ግን ከኬሚካሉ ጋር ስማቸው ይነሳል።

ሕንድ

በትንሹ 740 ቶን የሚሆን አሞኒየም ናይትሬት በ37 ኮንቴይነር ውስጥ ቺናይ ከሚባለው ከተማዋ በ20 ኪሎ ሜትር ርቆ፣ ተከማችቶ ይገኛል።

መጋዘኑ የሚገኘው ከመኖሪያ መንደር በ700 ሜትር ብቻ ርቀት ላይ ነው።

እዚያ ሰፈር ከተቀመጠ አሁን አምስት ዓመት ሊያልፈው ነው። ቤይሩት የፈነዳው ከስድስት ዓመታት ክምችት በኋላ መሆኑን ልብ ይሏል።

አሁን የአካባቢው ባለሥልጣናት ኬሚካሉን ከደቡብ ኮሪያ ካስመጣው ኩባንያ ጋር ፍርድ ቤት እየተካሰሱ ነው።

ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደረሰበት ምክንያት ደግሞ ኩባንያው ኬሚካሉትን ያስመጣው ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው ነው።

ኬሚካሉን ለማይታወቁ አካላት እንደሚቸበችውም ተደርሶበታል።

ዩናይትድ ኪንግደም

አንድ ምርመራ እንዳረጋገጠው ኬሚካሉ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ሐምበር ክልል፣ በኢሚንግሀማ ሊንከንሻየር ወደብ ውስጥ ይገኛል።

የብሪቲሽ ወደቦች ማኅበር እንዳስጠነቀቀው የአገሪቱ ወደቦች አስፈላጊውን ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የመን

በኤደን ወደብ መቶ ካርጎ አሞኒየም ናይትሬት ተከማችቷል የሚል ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ የየመን ዐቃቢ ሕግ ምርመራ እንዲጀመር አዘዋል።

ኬሚካሉ ወደ ኤደን ወደብ ከገባ ሦስት ዓመት አልፎታል ተብሏል። ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የተያዘውም በሳኡዲ መራሹ ኃይል አማካኝነት ነው።

የኤደን ገዥ ጣሪቅ ሳላም "ለዚህ ተጠያ የሚሆኑት ታጣቂ ኃይሎች ናቸው" ብለዋል።

130 የመርከብ መጋዘን ሙሉ የተከማቸው ይህ ኬሚካል 5ሺህ ቶን ገደማ ይመዝናል።

የየመን የኤደን ባሕረ ሰላጤ ወደቦች ኮርፖሬሽን እንደሚለው ግን የተከማቸው ኬሚካል አገልግሎቱ ለማዳበሪያ ሲሆን ምንም የተቀጣጣይነትም ሆነ የጨረራማነት አደጋን አያስከትልም።

"ማከማቸቱ አልተከለከለም፤ ችግርም የለውም፤ ተረጋጉ" ብለዋል።

ኢራቅ

የቤይሩቱን ጥፋት የተመለከቱት የኢራቅ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሁሉም ወደቦች አካባቢ የሚገኙ ኬሚካሎች ላይ ፍተሻ እንዲደረግ አዘዋል።

ከዚህ ቀደም በባግዳድ አየር መንገድ መጋዘን ውስጥ ይህ ኬሚካል ተከማችቶ ይገኝ ነበር።

ከትናንት በስቲያ አንድ የወታደራዊ ዕዝ በትዊተር ሰሌዳው ላይ እንደገለጸው የኢራቅ መከላከያ ሚኒስቴር ይህንን አደገኛ ኬሚካል ከባግዳድ አየር መንገድ ወደ ሌላ ቦታ ወስዶታል።

አውስትራሊያ

ከሳምንት በፊት በቤይሩት የደረሰውን ፍንዳታ ገና ከመድረሱ ቀደም ብሎ በአውስትራሊያ ኒውካስል እና በኒው ሳውዝ ዌልስ የሚገኙ ሰዎች በ3 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው ይህ ኬሚካል ገለል እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ ነበር።

ነገር ግን ኦሪካ የተሰኘውና ለማዕድን ኩባንያዎች ይህንን ኬሚካል የሚያቀርበው ኩባንያ "ምንም አስጊ ነገር የለም። በልዩ ጥንቃቄ ነው የተቀመጠው፣ መጋዘኑንም እሳት በማያነደው ቁስ ነው የገነባነው" ብሏል።

የደቡብ አውስትራሊያ የሥራ ቦታ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንዳለው ከሆነ በአሁኑ ሰዓት አሞኒየም ናይትሬት በአውስትራሊያ 170 መጋዘኖች ውስጥ በጥብቅ ጥንቃቄና ክትትል ተከማችቶ ይገኛል።