ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊባኖስ፡ ለቤይሩቱ ፍንዳታ ምክንያት የሆነችው የምስጢራዊዋ አሮጌ መርከብ ታሪክ
ሰዎች የሸጎሌን ወይም የበቅሎ ቤት ፍንዳታን ያስባሉ። ይህ ነገሩን በእጅጉ ማቅለል ነው የሚሆነው። በቅሎ ቤት ሲፈነዳ አዳማ ድረስ ንቅናቄ አልተሰማም።
የሊባኖሱ ፍንዳታ ጎረቤት ቆጵሮስ ደሴት ድረስ ተሰምቷል። 240 ኪሎ ሜትር።
አሁን ጥያቄው ፍንዳታው መሬት-አርድ ነበር ወይስ አልነበረም አይደለም። የፈነዳው ምንድነው? ያፈነዳውስ ማን ነው? ለምን አሁን? እንደሚፈነዳ የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ?
እነዚህን ወሳኝ ጥያቄዎች ለመመለስ የአንዲት ከርካሳ አሮጊት መርከብን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል።
ማክሰኞ ዕለት
ሊባኖሳዊያን ከሥራ ወደ ቤት የሚገቡበት ሰዓት ተቃርቧል።
መጀመርያ የሊባኖስ መሬት በስሱ ተነቃነቀ። ቀጥሎ ሸብረክ ነገር አለ፤ አሁንም በስሱ።
ሰዎች እርስበርስ 'ምንድነው መሬቱ የተነቃነቀ አልመሰለህም?' ተባባሉ። "አይደለ? አዎ! እኔም…"
3-2-1….ቡምምምምምም!
ሊባኖሳዊያን በሕይወት ዘመናቸው ሰምተውት የማያውቁት ፍንዳታ ተሰማ።
ልብ በሉ፤ ሊባኖሳዊያን ለፍንዳታ አዲስ አይደሉም። ፍንዳታ ሰምተው የምን ስሪት ቦምብ እንደሆነ ሊነግሯችሁ የሚችሉ አዛውንቶች ያሉበት አገር ነው። ይህ ግን ይለያል።
ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። አንድ ነዋሪ ለሲኤንኤን ቴሌቪዥን "እኔ 'የውማል-ቂያማ' መስሎኝ ነበር" ብሏል። 'የውመል-ቂያማ' የአረብኛ ቃል ነው፤ የምጽአት ቀን ማለት ነው።
አቶሚክ ቦምብ ይሆን የፈነዳው?
እስካሁን ባለው መረጃ አሞኒየም ናይትሬት ክምችት ነው የፈነዳው። ድምጹ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ ከተጣለው አውቶሚክ ቦምብ ላይተናነስ ይችላል።
በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ እንደ ውሃ ፈሷል።
ይህ ማለት ቦሌ ፍንዳታው ተከስቶ ቢሆን ሸጎሌ መኪና እየነዳ ያለ ሰው ቆስሏል ማለት ነው።
ስለፍንዳታው ማን ያውቅ ነበር? ማንስ ተጠያቂ ነው? ለሚለው ጥያቄ ግን ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆኗል። የከርካሳዋ አሮጌ መርከብ ታሪክ ግን ፍንጭ ይሰጣል።
ማክሰኞ ማታ
ማክሰኞ ዕለት በሊባኖስ ቤይሩት ነገሩ ሁሉ ሲተረማመስ ነው ያመሸው።
ሰዎች ድምጽ እንደሰሙ እግራቸው ወደመራቸው ቦታ መሮጥ ጀመሩ። መኪና ያለው በመኪናው፣ እግር ያለው በእግሩ. . . እግሬ አውጪኝ. . .
ያን ድምጽ ሰምቶ ማን ይቆማል?
ማንም፤ ግን ወዴት እንደሚሸሽ እርግጠኛ አይደለም። ለምን እንደሚሸሽም የሚያውቅ የለም! ከማን እንደሚሸሽ የተረዳ የለም. . . መሮጥ፣ ማምለጥ. . . መራቅ. . .
ፍንዳታው አንድ ጊዜ ወደ ላይ ከጎነ በኋላ የሆነ መስጊዶች አናት ላይ የሚቀመጥ ጉልላት ዓይነት ቅርጽ ሰራ። ከዚያም መንኮሮኮር ሲመነጠቅ ያለ የስብቀት እሳት ፈጠረ. . . ከዚያ ንዳድ. . .
ሰማዩ በእሳት የሚያያዝ መሰለ።
ከአፍታ በኋላ አውራ ጎዳናዎች በሰዎችና በመኪኖች ተሞሉ። አምቡላንስ ማለፊያ አጣ። ሰዎች አደጋው ወደደረሰት አቅጣጫ ሩጫ ጀመሩ። ልጆቻቸውን፣ ባሎቻቸውን ሚስቶቻቸውን ፍለጋ. . . ።
አደጋው ደረሰበት ከተባለው አቅጣጫ ደግሞ ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ ላይ ያሉ ሰዎች እየሸሹ ነው። እንዴት ይተላለፉ። የቤይሩት ሰሜናዊ አውራ ጎዳና ተጨነቀ።
በዚህ መሀል ታዲያ አንዳንድ ሰዎች በደም ባሕር የዋኙ ይመስል ድንገት ከፍርስራሽ ስር እያቃሰቱ ይወጣሉ። ጣዕረ ሞት መስለው የሚንፏቀቁም ነበሩ። ነገሩ ፊልም ይመስል ነበር።
"ያ አላህ ልጄን!" እያሉ የሚያለቅሱ እናቶች. . . አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን አግኝተዋቸዋል። አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ እየፈለጉ ነው።
ይህ አሰቃቂ ፍንዳታ ዛሬ ማክሰኞ ሳምንት ሆነው።
ብዙ ሊባኖሳዊያን በቃ ጠፍተው ቀርተዋል ማለት ነው። ምናልባት እሳት በልቷቸዋል. . . ። ምናልባት ፍንዳታው ሰማይ አድርሶ መልሶ ቀብሯቸዋል።
ይህ ሁሉ ትርምስ በምን እንደተፈጠረ የሚያውቅ አልነበረም። የዓለም መገናኛ ብዙሃን ስለ ፍንዳታው በደቂቃዎች ውስጥ የቀጥታ ሥርጭት ማስተላልፍ ቢጀምሩም ፈነዳ ይላሉ እንጂ ምን እንደፈነዳ አያውቁም ነበር።
እንኳን ያኔ፣ አሁንስ ማን እርግጡን አወቀ?
በሞባይል የተቀረጹ ምስሎች
11፡54 ላይ የሎስአንጀለስ ታይምስ ዘጋቢ በትዊተር ሰሌዳው ላይ ከደቂቃዎች በፊት በስልኩ ያስቀረውን ቪዲዮ አጋራ።
ነገሩ እሳት አደጋ ነው። እሳቱ የነካው ንጥረ ነገር ግን እጅግ አደገኛና ተቀጣጣይ ነበር። ርችት መጋዘኑ ውስጥ ሳይከማች አልቀረም።
የመጀመሪያው ፍንዳታን ተከትሎ ከ35 ሰከንዶች በኋላ ሌላ ፍንዳታ ተከስቷል። የሁለተኛው ፍንዳታ ቀይ ፍም እሳትና ቡኒ ጭስ የያዘ ነበር።
በመቶዎች ሞተው ሺህዎች የቆሰሉትም በዚህ በሁለተኛው ፍንዳታ ሳይሆን አይቀርም።
የሁለተኛው ፍንዳታ ለቦምብ መቀመሚያነት የሚውለው የአሞኒየም ናይትሬት ክምችት ነበር ተብሎ ይገመታል።
በዚያ የወደብ መጋዘን ውስጥ ወደ 3ሺህ ቶን አሞኒየም ናይትሬት ተከማችቶ ነበር።
አሁንም ምን እንደፈነዳ? ምን እንደሆነ የሊባኖስ ርዕሰ ብሔርም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን ዳያብ እርግጡን አያውቁም።
ሁሉም ግን የአሮጌዋን መርከብ ታሪክ ያውቃሉ። ለቆራሌ ያልተሸጠችው ከርካሳ መርከብ።
ለቆራሌው ያልተሸጠችው መርከብ
ሮሰስ (Rhosus) ትባላለች፤ ግዙፍ መርከብ ናት። ማንም ግን አይፈልጋትም፣ ከቆራሌው በስተቀር። ለምን?
እዚህ ፎቶ ላይ የሚታዩት ሁለቱ ሰዎች ይህን ፎቶ የተነሱት በፈረንጆቹ 2014 በጋ ላይ ነበር።
ከጀርባቸው በነጭ ጆንያ የታጨቀው ነገር ይታያችኋል? የእርዳታ በቆሎ የሚመስለው? እሱ 3ሺህ ቶን የሚዝን አሞኒየም ናይትሬት ነው። በጣም አደገኛ ኬሚካል።
በግማሽ ፈገግ ብሎ ስልክ እያወራ የምታዩት ሰውዬ ባለ ብዙ ሐሳብ ነው።
የዚች ከርካሳ መርከብ ካፒቴን እሱ ነው። ከዩክሬን ነው የመጣው። በዚያን ጊዜ እሱም ሆነ የመርከቧ ሠራተኞች በቤይሩት ታግተው ነበር። ስልክ የሚደዋውለው ጨንቆት ነው።
ለምን?
ታሪኩን ትንሽ ወደ ኋላ ሸርተት ብለን ካልጀመርን ግልጽ አይሆንም።
መርከቧ ከጆርጂያ ነው የተነሳቸው።
ይቺ ጦሰኛ መርከብ በመስከረም 2013 ነበር ከጆርጂያ፣ ባቱሚ ወደብ የተነሳችው። ወዴት ለመሄድ ካላችሁ ወደ ሞዛምቢክ። ወደ አፍሪካዊቷ አገር ደግሞ ምን ልትሰራበት ነው የምትሄደው? ካላችሁ እቃ ተልካ። ይህን አሞኒየም ናይትሬት ጭነሽ ነይ ተብላ።
መርከቧ ከርካሳ ናት ብለናል። ይህን በፎቶ አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል።
አሮጊቷ መርከብ በ1986 ነው የተሠራችው። እድሳት ብሎ ነገር አታውቅም ታዲያ።
ዓመታዊ ቦሎ የምታስለጥፈው አጭበርብራ ነው እንጂ ወላልቃለች። መኪና ብትሆን የምትነሳው በግፊ ነው ማለት ይቻላል።
የመርከቢቱ ባለቤት ቆጵሮስ የሚኖር ሩሲያዊ ነጋዴ ነው። ስሙም ኢጎር ግሪኩሽኪን ይባላል።
ይቺ ከርካሳ መርከብ ከጆርጂያ፣ ባቱሚ ወደብ የተነሳችው ምን ጭና ነው አልን?
ቢቢሲ እጅ የገባ አንድ መርከብ ላይ የሚጫን እቃ ዝርዝር የሚጻፍበት ሰነድ (ቢል ኦፍ ሎዲንግ) እንደሚያስረዳው መርከቧ አሞኒየም ናይትሬት ነበር የተጫነባት።
ኬሚካሉን የጫነው ድርጅት ሩስታቪ አዞት (Rustavi Azot LLC) የተባለ አሞኒየም ናይትሬት አቅራቢ ነው። ይህ ኩባንያ አሞኒየም ናይትሬቱን ለማን ነው የሚያቀርበው? ከተባለ ለኢንተርናሽናል ባንክ ኦፍ ሞዛምቢክ ነው። ተቀባይ ሆኖ የተመዘገበውም ይህ ባንክ ነው።
ባንክ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ፈንጂ መቀመሚያ አሞኒየም ናይትሬት የሚያዘው? ደግሞስ ምን ይሠራለታል? ካላችሁ ነገሩ ወዲህ ነው።
ዕቃ ወደ አንድ አገር በመርከብ ሲጫን ዋስ ሆነው የሚመዘገቡት ባንኮች ናቸው። ስለዚህ የሞዛምቢክ ባንክ ወኪል ሆኖ ዕቃውን የሚቀበልለት ድርጅት አንድ ትንሽ የሞዛምቢክ ፈንጂ አምራች ኩባንያ ነው። የዚህ ኩባንያ ሥራ ሌላ ሳይሆን ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ማምረት ነው።
ይህቺን ከርካሳ መርከብ ይሾፍሯት የነበሩት ካፒቴን ፕሮኮቼቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እርሳቸው መርከቧን የተረከቡት ከቱርክ ወደብ ነው።
የመርከቧ ባለቤት ለመርከበኞቹ ደመወዝ መክፈል ስላልቻለ ሁሉም ጥለውት ሄደው ነበር።
ካፒቴኑ አቴንስ መልህቃቸውን ጥለው አዳዲስ መርከበኞችን ሰብስበው ተቀመጡ። ጉዞ ለምን አይጀምሩም ታዲያ ወደ ሞዛምቢክ?
ምክምያቱም የመርከቧ ባለቤት ብር አልነበረውም። ስዊዝ ካናል ሲደርስ ለወደብ የሚከፍለው ብር የለውም።
"እንሂድ? ሞልታለች እኮ መርከቧ" ሲባል "ቆይ ብር የለኝም፤ ተረጋጉ" ይላል።
ታዲያ ምን ይሻላል? ሲባል፣ "በቃ ቆይ ትንሽ እንታገስና መንገድ ላይ ሌላ ትርፍ የሚጫን ካርጎ እስክናገኝ እንጠብቅ።"
በዚህ ሁኔታ አራት ወራት አለፉ። ከጆርጂያ ወደ ሞዛምቢክ ወደብ ልትጓዝ የነበረችው መርከብ በአቴንስ አራት ወር አንቀላፋች።
እንዴት ወደ ቤይሩት ወደብ ሄደች ታዲያ?
ከዕለታት አንድ ቀን ታዲያ 'ሽቀላ' ተገኘ ተባለ። የት? ሲባል፣ ቤይሩት ወደብ ላይ።
አስቡት እንግዲህ፣ ወደ ሞዛምቢክ እቃ የጫነ መርከብ ሌላ ትርፍ ዕቃ ለመጫን አራት ወር ቆሞ ወደ ቤይሩት ሲያመራ።
የመርከቧ ባለቤት ከቆጵሮስ ሆኖ ባስተላለፈው ትዕዛዝ ጉዞ ወደ ቤይሩት ሆነ።
በቤይሩት ጥሩ የወደብ መክፈያ ገንዘብ ያስገባል የተባለው ካርጎ የታጨቀው የግንባታ መሣሪያዎችን ነበር። እሱን በከርካሳዋ መርከብ ጭኖ ወደ ሞዛምቢክ ለመሄድ ነው የሁሉም ሐሳብ።
በስንት መከራ ቤይሩት ወደብ ደረሱ። ይህ ሁሉ የሚሆነው የዛሬ ስድስት ዓመት በኅዳር ወር ላይ ነው።
"ቤይሩት ደርሰን ጭነቱን ስናየው ግዙፍ ነው። መርከቧ ላይ ስንጭነው ከርካሳዋ መርከብ መንጣጣት ጀመረች። ከአቅሟ በላይ ነበረ። ትርፍ ካርጎ ለመጫን የሚሆን ጫንቃ አልነበራትም" ይላሉ የመርከቧ ካፒቴን፤ ወደ ኋላ በትዝታ ተመልሰው።
"በቃ እኔ ይሄ በፍጹም አይሆንም፤ ሁላችንም እናልቃለን። መርከቡ ካርጎውን አይችለውም አልኩኝ፤ ወሰንኩኝ" ይላሉ ካፒቴኑ።
ለመርከቧ ባለቤት ተደወለ። እና ምን ይሻላል. . . ?
ዝም አለ።
በቃ የመርከቧ ባለቤት የወደኖርባት ቆጵሮስ ሄደን እሱኑ እናማክረው ይሉና መርከቧን ማንቀሳቀስ ሲጀምሩ የሊባኖስ ባለሥልጣናት መጥተው "ወዴት. . . ወዴት?" ይሏቸዋል።
"አይ እዚህ ካርጎ ልንጭን መጥተን ካርጎው ትልቅ ሆነብንና ይቺ ከርካሳ መርከብ አልቻለችውም፤ እና ተውነው" ይላሉ።
"እና የኮቴ ክፈሏ፤ የመርከብ ኮቴ፤ የገባችሁበትን ክፈሉ" በማለት የወደቧ ፖሊሶች አፈጠጡባቸው።
"ምንም ሳንጭን? ካርጎውን አልጫንም እኮ. . . " ካፒቴኑ ተከራከሩ።
የተራ አስከባሪና የረዳት ጭቅጭቅ ተጀመረ።
ለካንስ መርከቧ ለሊባኖስ ያልከፈለችው መቶ ሺህ ዶላር እዳ ነበረባት።
"እኛ ሠራተኞች ነን፤ ምን እናድርግ ብንላቸውም የቤይሩት ባለሥልጣናት አሻፈረኝ አሉ። እዳ አለባቸሁ ክፈሉ።"
ነገሩ ሽማግሌ ገባበት መሰለኝ በኋላ ላይ አብዛኞቹ መርከበኞች ተለቀቁና ካፒቴኑን ጨምሮ አራት የመርከቢቷ ኢንጂነሮች ብቻ ታገቱ። በአጋጣሚ ሁሉም የዩክሬን ዜጎች ናቸው።
የታገቱት ካፒቴን እንዴት ተለቀቁ?
"ሌባኖሶች እኛን እንደ መያዣ አድርገው አገቱን፤ እዳ ካልተከፈለ አንለቃችሁም አሉ።"
ካፒቴን ፕሮኮቼቭ ግራ ገባቸው።
ቢጨንቃቸው ለቭላድሚር ፑቲን ደብዳቤ ጻፉ። መልስ የለም።
በቤይሩት ለሩሲያ ቁንስላ ጉዳዩን አመለከቱ። ተሳለቁባቸው። "ፑቲን ልዩ ኃይል አስልኮ እንዲያስፈታህ ነው የምትፈልገው?"
ካፒቴኑ ዩክሬናዊ ሆነው ለፑቲን ደብዳቤ የሚጽፉት፤ የመርከቧ ባለቤት ሩሲያዊ ስለሆነ ነው።
ወይም ደግሞ ከፑቲን ሌላ ይህን ችግር የሚፈታ ጉልበተኛ የለም ብለው አስበውም ይሆናል።
ነገሩ እየተካረረ መጥቶ የአራቱ ታጋቾች ጉዳይ የዓለም የትራንስፖርት ሠራተኞች ፌዴሬሽን ጋር ደረሰ።
ጉዳዩን የመረመረችው የፌዴሬሽኑ አለቃ በመጋቢት 18/2014 በጻፈችው ደብዳቤ እንዳረጋገጠችው የመርከቧ ባለቤት ሩሲያዊው ኢጎር ግሪኮሽኪን እዳውን ለመክፈል ቤሳቤስቲን የለውም፤ ከስሯል።
. . . ከዚህ በላይ ደግሞ አሳሳቢው ከርካሳዋ መርከብ የጫነችው አደገኛው አሞኒየም ናይትሬት የተባለው ኬሚካል ነው። የቤይሩት ወደብ ኃላፊዎች ይህ ንጥረ ነገር የተጫነውን ካርጎ ወደየትም እንዳይንቀሳቀስ አግደዋል። ይህ አደገኛ ነው" ስትል ጻፈች።
ከአራት ወራት በኋላ ደግሞ ፍሊትሞን በተባለ አንድ የንግድ ጉዳዮች መጽሔት ላይ እንዲህ የሚል ዜና ወጣ።
"ቦምብ እየተንሳፈፈባት ባለች መርከብ ውስጥ የታገቱ መርከበኞች"
ይህ ሁሉ የሆነው ታዲያ የዛሬ ስድስት ዓመት በሐምሌ መጨረሻ ሳምነት ላይ ነበር።
እንደሚፈነዳ ነግረናቸው ነበር…
እነ ካፒቴን ፕሮኮቼቭ ከቤይሩት ራሳቸውን እንዴት ነጻ ያውጡ?
አራት ሆነው ሰልፍ ቢወጡ፣ እገታውን ለሚዲያ ቢናገሩ. . . ጠብ የሚል ነገር የለም።
ቢጨንቃቸው የመርከቢቱን ነዳጅ እየቀዱ መሸጥ ጀመሩ። ነዳጁን ቀሽበው በሚያገኙት ገንዘብ ጠበቃ ቀጠሩ።
ከ10 ወራት የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ ነጻ ወጡ።
ጭንቀታችን የነበረው ከርካሳዋን መርከብ ውስጧ ውሃ እንዳይነካትና ደረቅ ሆና እንድትቆይ ማድረግ ነበር። ምክንያቱም የጫነችው አደገኛ ኬሚካል ነዋ። ይህ ግን የቤይሩት ሰዎችን በዚያን ጊዜ ብዙም አላስጨነቃቸውም። እነሱን ያስጨነቃቸው የመርከቢቱ እዳ አለመከፈሉ ብቻ ነው።
"ነግረናቸው ነበር. . . "ይላሉ ካፒቴኑ። "ግን አልሰሙንም።"
ካፒቴኑ ከቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ጋር አደጋው በደረሰ ማግስት ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት "ቤይሩቶች ያን ጊዜ እዳችንን ክፈሉ ብለው እኛን ከሚያግቱን የመርከቧን እዳ ራሳቸው ከፍለው ያቺን መርከብ ከወደባቸው ቶሎ አስወጥተው የሰላም እንቅልፍ ቢተኙ ይሻላቸው ነበር።"
ካፒቴን ፕሮኮቼቭ ፍርድ ቤት ነጻ ሲያደርጋቸው መርከቢቱን ቆላልፈው፣ የብረት መዝጊያውን ገጥመው ቁልፍ ለቤይሩት የወደብ ባለሥልጣናት አስረክበው ነው የሄዱት።
ይህም በመስከረም 2014 ነው የሆነው።
ያቺ ከርካሳ መርከብ ታዲያ ከዚያን ወዲያ ቆራሌውም ሳይወስዳት፣ ባለቤቷም የት ነሽ ሳይላት፣ መርከበኞቿም ረስተዋት ሰምጣ ቀረች።
ዛሬም ድረስ የት እንዳለች የሚያውቅ የለም።
ኬሚካሉ ለሊባኖስ ገበሬ ቢሰጥ ኖሮ
ከአደጋው በኋላ ካፒቴን ከራዲዮ ሊበርቲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቤይሩት ባለሥልጣናት ለፍንዳታው ብቸኛዎቹ ተጠያቂዎች ናቸው ብለዋል።
"አንድ መርከብ ባለቤት ከሌለው፣ በቃ የለውም ነው። ካርጎውን ማስወገድ ነበረባቸው፣ ወይም ደግሞ ለሊባኖስ ገበሬ ኬሚካሉን ቢያድሉት ኖሮ ይሄ አደጋ ባልደረሰ ነበር።"
ለመርከበኞቹ ያኔ በታገቱ ጊዜ ጥብቅና ቆመውላቸው ከነበሩ ነገረ ፈጆች አንዱ እንደተናገረው፤ ደንበኞቻችን በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ካቀረብናቸው ምክንያቶች አንዱ የጫኑት ነገር ለሕይወታቸው አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል በመጥቀስ ነው።
ያን ጊዜ ለፍርድ ቤት ከጻፉት ማስታወሻ የተቀነጨበው እንዲህ ይላል. . .
"መርከቡን ካርጎው አሞኒየም ናይትሬት ኬሚካል መጫናቸው ከግምት ውስጥ ገብቶ ይህ ኬሚካል ወደ ወደቡ መጋዘን እንዲገባ መርከቡም ሆነ ካርጎው በጨረታ አልያም በጥንቃቄ እንዲወገድ. . ."
ዋናው ተጠያቂ ማነው?
አሞኒየም ናይትሬት የናይትሮጂን ማዳበርያ ሆኖ በስፋት ለገበሬዎች አገልግሏል። ነገር ግን ይህ ኬሚካል ለሚቀበር ፈንጂ መሥሪያነት በስፋት ይውላል።
ለዚያም ነው መጀመሪያ ፍንዳታውን በአንጻራዊ ቅርበት የሰሙ ኑክሌር ቦምብ የመሰላቸው።
የማክሰኞው ፍንዳታ መጠነ ንዝረት ሲለካ እስከ 2 ኪሎ ቶን ይሆናል። ሂሮሺማና ናጋሳኪ ላይ አሜሪካ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ዋዜማ የጣለችው ቦምብ መጠነ-ንዝረቱ 12 ኪሎ ቶን ይሆናል።
ኬሚካሉ ሲፈነዳ ቀይ ነገር በጭስ መልክ ሲተን ታይቷል። ቀዩ ትነት መርዛማው ናይትሮጂንዳይኦክሳይድ ነው።
የፍንዳታው የንዝረት ፍጥነት ደግሞ ሱፐርሶኒክ ነው። 'ሱፐርሶኒክ' ፍጥነት ማለት ከድምጽ የሚፈጥን ማለት ነው።
እንዴት ሊፈነዳ ቻለ? ማን አፈነዳው? ወደሚለው ወደተነሳንበት ነጥብ እንመለስ።
አሞኒየም ናይትሬት ወትሮም መከማቸት ካለበት ከተማ ውስጥ አይቀመጥም። ሰው ከማይደርስበት ተራራ እንጂ።
ሆኖም ግን በራሱ ጊዜ ፈንድቶ የሚጎን ኬሚካል ነው ማለት ደግሞ አይደለም። አንድ ነገር ሊያቀጣጥለው ይገባል።
የቤይሩቱን ፍንዳታ ምን ቆሰቀሰው ለሚለው ግን አሁንም መልስ አልተገኘም።
የቤይሩቱ ፍንዳታ ሁለት ምዕራፍ ነበረው። የዓይን እማኞች እንደሚሉት የመጀመሪያው ልክ እንደ ርችት ያለ ነበር። ሁለተኛው ግን ምድር-አርድ ነበር።
የወደቡ የጉምሩክ ኃላፊ በድሪ ዳሃር በሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን ላይ "በወደቡ መጋዘን ውስጥ የርችት ክምችት ነበረ ወይ?" ተብለው ሲጠየቁ፤ "ይመስለኛል" ብለዋል።
ሌሎች ምንጮች ደግሞ በወደቡ ብረት እያቀለጡ መገጣጠሚያ የመሥራት ሂደት (ብየዳ) ሲከናወን ነበር ብለዋል። እሳቱ ምናልባት ከብደየዳ ፍንጣሪ መንጭቶ ይሆናል።
የወደቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐሰን ኮራይተም ለሚዲያ እንዳመኑት "የአገሪቱ የደኅንነት ሰዎች የመጋዘኑን በር እንድንሰራው አዘውን፤ ሥራውን ቀትር ላይ ጨርሰን ሄድን፤ ከሰዓት ምን እንደተፈጠረ አላውቅም" ብለዋል።
እሳቱ በምንም ይነሳ በምን ብቻ ወዲያውኑ 10 የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ወደ ቦታው አቅንተው ነበር። መጋዘን ቁጥር-12 ደርሰውም ነበር።
ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ሴት ነበረች። አሁን አስሩም የት እንዳሉ የሚያውቅ የለም። ከዚያ ፍንዳታ ይተርፋሉ ማለት ተአምር ነው መቼስ።
የወደቡ ኃላፊዎች ቦምብ በመጋዘናቸው እንዳለ ካወቁ 6 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ተራ ዜጎች ይህን የሰሙት ግን ማክሰኞ ማምሻውን ነው።
አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች የወደቡ ኃላፊዎች ከ2014 እስከ 2017 ድረስ አራት ደብዳቤዎችን ለአስቸኳይ ጉዳይ የዳኞች ሸንጎ ጽፈዋል።
ደብዳቤዎቹ የሚሉት "ይሄ ኬሚካል ተቀጣጣይ ስለሆነ ወይ ውጭ አገር ወስደን እንሽጠው ወይ እናስወግደው፤ ፍቀዱልን" ነው።
አንዳንድ ሊባኖሳዊያን እነዚህን ደብዳቤዎች ከተመለከቱ በኋላ የወደቡ ኃላፊዎች የሚችሉትን እንዳደረጉ ያስባሉ። ነገሩ ግን ውስብስብ ነው።
ሪያድ ቆባሲስ በሊባኖስ ሙስና በማጋለጥ ስመጥር ጋዜጠኛ ነው። አደጋው ከደረሰ በኋላ በቴሌቪዥን ቀርቦ እንደተናገረው አራቱም ደብዳቤዎች ሕጋዊ የሥልጣን ተዋረድን ጠብቀው የተጻፉ አልነበሩም። ዳኞችም ደብዳቤዎቹ ሁሉንም መረጃ አሟልተው እንዲጻፉ በተደጋጋሚ ጠይቀው ነበር።
የቤይሩት ወደብ ኃላፊዎች ግን የጻፉትን ደብዳቤ መልሰው ቀኑን እየቀያየሩ ይልኩታል።
ሊባኖስ በሐይማኖት መስመር ነው ሥልጣን የምታደላድለው፤ በአንዳንድ አገሮች ሙሰኞች ወንጀል ሰርተው ወደ ጎሳቸው ጉያ እንደሚደበቁት በሊባኖስ ፖለቲከኞች ቶሎ ወደ ሐይማኖት ቀፏቸው ይሸሸጋሉ።
የሊባኖስ ገንዘብ 80 ከመቶ ጋሽቧል። ሥራ የለም፤ ኑሮ እንደ ወደቡ ፍንዳታ ተተኩሷል።
አንዳንድ ሊባኖሳዊያን ታዲያ ምርር ብሏቸዋል። እንኳንም ፈነዳን ያሉ "ጨካኞችም" አልጠፉም።
"ምነው! ምነው! እንዲህ ይባላል?" ሲባሉ "ካልደፈረሰ አይጠራም" ብለው ይመልሳሉ።
ከዚህ በላይ ምሬት ከየት ይመጣል?