ሞቱ አሁንም ምስጢር የሆነው የቦሊውድ ፈርጥ

ሱሻንት ሲንግ ራይፑት ልክ እንደ እንደሚተውናቸው ገፀ-ባሕርያት አስደናዊ ሕይወት ያሳለፈ ሰው ነው።

ነገር ግን ልብ-ወለድ የሚመስለው ሕይወት - ከድህነት ወደ እንቁ የቦሊውድ ሰው ያደረገው ጉዞ - ሰኔ 7 ሊቋጭ ግድ ሆኗል።

የ34 ዓመቱ የቦሊውድ ተዋናይ በመኖሪያ ቤቱ ሞቶ ተገኘ። የሙምባይ ፖሊስ የሞቱ ምክንያት ራስን ማጥፋት ነው ሲል አስደናጋጭ ዜና ለአደናቂዎቹ አወጀ።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎቹ ዜናውን አሁንም ማመን አቅቷቸዋል።

ሱሻንት ቢሃር በተሰኘችው ደሃ የሕንድ ግዛት ነው ያደገው። ሱሻንት የሃገሪቱ ከፍተኛ የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ለመግባት ጠንክሮ መሥራት ነበረበት።

ወጣቱ ሕንድ ውስጥ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ቁልፍ ነው ወደ ተባለለት ኮሌጅ ቢገባም ልቡ ቦሊውድ ነበረች። ይሄኔ ነው ትምህርቱን አቋርጦ ሕልም ጠግና ወደምትሰራው ሙምባይ ያቀናው።

ለዓመታት ትናንሽ የሚባሉ ገፀ-ባሕርያትን እየተጫወተ ወደ ቦሊውድ ጣራ የሚያደርሰውን አሳንሰር ይጠባበቅ ጀመረ። በስተመጨረሻም እሱ ይተውንበት የነበረ አንድ የቴሌቪዥን ድራማ የሕንዳውያን መነጋገሪያ ሆነ።

የሱሻንት ታሪክ ለብዙዎች እንደ ምሳሌ የሚቀርብ ነው። ሕንዳውያን ወላጆች ለልጆቻቸው የሚተርኩት። ለዚህም ነው የሱሻንት ሞት ለብዙዎች አስደንጋጭ ዜና ሆኖ የመጣው።

ከሞቱ በኋላ እየተሰሙ ያሉ ዜናዎች ደግሞ የሱሻንት ሞት ምክንያት አሁንም ምስጢር አድርገውታል። የሱሻንት የነበረው ገንዘብ፣ የፍቅር ሕይወቱ እንዲሁም የአእምሮ ጤናውን የሚመለከቱ ዘገባዎች ወጣ ወጣ ማለት ጀምረዋል።

የአእምሮ ጤና አማካሪው፣ ምግብ አብሳዩ፣ ጓደኞቹ፣ ወኪሉ፣ ቤተሰቦቹ፣ የሥራ አጋሮቹ በሕንድ ሚድያዎች እየተፈገሉ ነው። መገናኛ ብዙሃን ከፖሊስ የሚያገኟትን ጥቃቅን መረጃዎች በመያዝ ይህ እውነት ነው ወይ ሲሉ ስልክ ያንቃጭላሉ።

የሱሻንት ሞት ምክንያት ከመጥራት ይልቅ እየደፈረሰ መጥቷል።

ሱሻንት ከሞተ ጥቂት ቀናት በኋላ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ተዋናዩ ራሱን ያጠፋው ቦሊውድ ውስጥ ያሉ ኃያላን የሚገባውን ክብር ስላልሰጡት ነው ማለት ጀመሩ።

ተዋናዩ ብዙዎች ባላሰቡት መንገድ ወደ ዝና ስለመጣ በቦሊውድ ኃያላን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፤ አልፎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትላልቅ ፊልሞች ላይ እየተሳተፈ አይደለም የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።

የተዋናዩ አድናቂዎች አንዳንድ የቦሊውድ ፊልም ዳይሬክተሮችን ዒላማ አድርገዋል። ከእነዚህ መካከል ካራን ጆሃር አንዱ ነው። ፖሊስ ሰውዬውን እስካሁን አልጠየቀውም። ቢሆንም የሱሻንት አድናቂዎች ዛቻ ሁላ እየሰነዘሩበት ነው።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ፊልም ነቃሽ ወቃሽ [ክሪቲክ] የተዋናዩ ሞት ቦሊውድ ውስጥ ጥሩ ትስስር የሌላቸው ሰዎች ቦታ እንደሌላቸው የሚያሳይ መራር ሃቅ ነው ይላል። ቢሆንም የፖሊስን ምርመራ ውጤት መጠበቅ ግድ ነው ሲል ያክላል።

የተዋናዩ ፍቅረኛ የነበረችው ተዋናይት ቻክራቦርቲ ሌላኛው የዘገባዎች ዒላማ ነች።

የሱሻንት ቤተሰብ አባላት ተዋናይቷን ያላቸውን ቅሬታ ለፖሊስ አሰምተዋል። አባት፤ ወደ ራስ ማጥፋት የገፋችው አሷ ናት፤ ለገንዘብ ማባከንም ዳርጋዋለች ሲሉ ይወቅሳሉ።

በዚህም ምክንያት ከማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችና ከመገናኛ ብዙሃን ብዙ ጫና እየደረሰባት ይገኛል።

የተዋናዩ የባንክ ሒሳብ ደብተር ዝርዝር ሾልኮ ወጥቶ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል። የአእምሮ ጤናውን የተመለከቱ መረጃዎችም ወጥተዋል።

ሱሻንት ማሕበራዊ ሚድያዎች ላይ በርካታ ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። የተዋናዩ የጤና አማካሪ በመገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ የተሰማቸውን ሃዘኔታ ይገልፃሉ። በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተከታዮቹ ይህ ተገቢ አይደለምም ይላሉ።

ፖሊስም ያገኛቸውን መረጃዎች ሁሉ ለሚድያ አሳልፎ በመስጠት ተወቅሷል።

ሕንድ ውስጥ የአእምሮ ጤና ጉዳይ የተዳፈነ ፍም ነው።

የሙምባይ ፖሊስ አሁንም ምርመራውን ቀጥሏል። እስካሁን ከ50 በላይ ሰዎች ቃለ-መጠይቅ ተድርጎላቸዋል። ነገር ግን እስካሁን ምንም ዓይነት የተጨበጠ የምርመራ ውጤት ይፋ አላደረገም።