ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንዱ የአውሮፕላን አደጋ የሟቾች ቁጥር 18 ደረሰ
የኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በደቡባዊ ሕንድ ኬሬላ ግዛት በሚገኝ አየር ማረፊያ ባጋጠመው አደጋ ቢያንስ 18 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
190 ሰዎችን አሳፍሮ ከዱባይ የተነሳው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ላኪከት አየር ማረፊያ ሲደርስ በነበረው ዝናብ ምክንያት ከማኮብኮብያው አስፋልት ተንሸራቶ ወጥቶ ነው የተከሰከሰው።
አውሮፕላኑ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዱባይ ውስጥ ለወራት መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሕንዳውያንን አሳፍሮ ነበር።
ጠለቅይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በተፈጠረው አደጋ 'ሕመም' እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአደጋው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን እንዲሁም የተረፉ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል ወስደዋል። 15 ሰዎች ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው፤ በርካቶች ቀላል የሚባል አደጋ ነው ያጋጠማቸው ተብሏል።
ኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች አንደሆኑ ይፋ አድርጓል።
የበረራ ቁጥር አይኤክስ 1134፤ 10 ሕፃናትን ጨምሮ 184 መንገደኞችና 6 የአውሮፕላኑን ሠራተኞች አሳፍሮ ነበር።
አውሮፕላኑ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 1፡40 ነው የተከሰከሰው። በወቅቱ በሥፍራው ከባድ ዝናብ እየጣለ ነበር ተብሏል። አብራሪዎቹ መጀመሪያ ለማረፍ ያደረጉት ሙከራ በዝናብ ምክንያት በማቋረጥ ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት ሙከራ ነው አደጋው የተከሰተው።
የሕንድ ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ሃርዲፕ ሲንግ ፑሪ የአጋውን ኦፊሴላዊ ምክንያት በምርመራ ቡድን አባላት እንደሚጣራ አሳውቀዋል።
ባለሥልጣናት፤ አውሮፕላኑ ለሁለት የተከፈለው ከመንደርደሪያው ውጭ ከነበረ አንድ ጎድጎድ ካለ ሥፍራ ጋር በመጋጨቱ ነው፤ በዚህም የአውሮፕላኑ ፊተኛው ክፍል በጣም መጎዳቱን አሳውቀዋል።
ነገር ግን አውሮፕላኑ እሣት ባለማስነሳቱ ምክንያት በርካቶች ሊተርፉ እንደቻሉ ታውቋል።
በሕንድ አሁን ወቅቱ ዝናባማ ነው። አውሮፕላኑ አደጋ ባጋጠመው አካባቢ ከቀናት በፊት በከባድ ዝናብ ምክንያት በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት ሰዎች እንደሞቱ ተዘግቦ ነበር።
በፈረንጆቹ 2010፤ የኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ አውሮፕላን በተመሳሳይ ከመንደርደሪያ ወጥቶ በተፈጠረ አደጋ 158 ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም።