ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድ፡ 190 ሰዎች አሳፍሮ በማረፍ ላይ የነበረ አውሮፕላን ተከሰከሰ
ንብረትነቱ የኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ የሆነው የበረራ ቁጥሩ IX-1344 የነበረው አውሮፕላን በሕንድ ደቡባዊ ግዛት ኬራላ በሚገኝ አየር ማረፊያ 190 ሰዎችን አሳፍሮ ለማረፍ ሲንደረደር መከስከሱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ከዱባይ የተነሳው አውሮፕላኑ በካሊከት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ በመንደርደር ላይ ሳለ ተንሸራቶ ለሁለት መከፈሉን የሕንድ አቪየሽን ባለሥልጣን ገልጿል።
በስፍራው የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተው ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ።
በአደጋው እስካሁን በትንሹ አብራሪውን ጨምሮ ሁለት ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ መንገደኞች መጎዳታቸውን የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ 10 ህፃናትን ጨምሮ 184 መንገደኞችን እንዲሁም ሁለት አብራሪዎችን ጨምሮ ስድስት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ነበር።
የሲቪል አቪየሽን ዳይሬክቶሬት ጀነራል አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ሰዓት ተንደርድሮ መቆሚያ መስመሩን ጨርሶ ሸለቆ ውስጥ በመውደቁ ለሁለት መከፈሉን ተናግረዋል።
የሕንድ መገናኛ ብዙኃን ያወጡት አደጋውን የሚያሳየው ምስልም አውሮፕላኑ ለሁለት መሰበሩን አሳይቷል።
አደጋው ያጋጠመው ከቀኑ 8፡30 አካባቢ ሲሆን በአካባቢው ከባድ ዝናብ እየዘነበ ነበር ተብሏል።
ሕንድ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት እያስከተለ መሆኑን ተናግራለች።
በሕንድ መሰል አደጋ ሲያጋጥምም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከ10 ዓመታት በፊት ግንቦት ወር ላይ ኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ አውሮፕላን በማንጋሎር አየር ማረፊያ ተንሸራቶ ባጋጠመው አደጋ የ158 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።