ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የብሪቲሽ ኤርወይስ ሠራተኞች ቁርጣቸውን የሚያውቁት ዛሬ ነው
የሠራተኛ ማህበራት 'ጥቁሩ አርብ' ሲሉ ሰይመውታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ለዓመታት ብሪቲሽ ኤርዌይስን ያገለገሉ የበረራ ሠራተኞች ቁርጣቸውን የሚያውቁበት ቀን ነው ዛሬ [አርብ]።
ከሥራ መባረር ቢቀርላቸው እንኳ ድመወዛቸው አናቱን ተመቶ ነው የሚደርሳቸው። ከቀጣሪ ድርጅታቸው ጋር ያላቸውም ግንኙነት እንደ ቀድሞ የሚሆን አይመስልም።
ኢንጂነሮችና ሌሎች የየብስ ስራውን የሚያከናውኑትን ጨምሮ የቢሮ ሠራተኞችም ከአየር መንገዱ ጋር መፃዒ ዕድል ይኑራቸው አይኑራቸው ቁርጡ የሚለየው ዛሬ ነው።
ብሪቲሽ ኤርዌይስ በበረራ ኢንዱስትሪ መቀጠል ካለብኝ ሠራተኞችን መቀነስ የግድ ይለኛል ያለው ከሳምንታት በፊት ነበር። ነገር ግን ይህን ለማድረግ የወሰነበር መንገድ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
"ከደመወዜ ላይ ግማሽ ያህሉ ሊቆረጥብኝ ይችላል" ትላለች የበረራ አስተናጋጇ ቪኪ።
"ብቻዬን ነው ልጅ የማሳድገው። እንዴት አድርጌ ነው 50 በመቶ ደመወዜን ዓይኔ እያየ የምሰጠው?"
ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሟን የቀየረችው ቪኪ በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ሲሆን ብሪቲሽ ኤርዌይስን [ቢኤ] ከ15 ዓመታት በላይ አገልግላለች።
ምንም እንኳ የምትኖረው ከአየር ማረፊያው ራቅ ብሎ በሰሜን ምስራቅ ለንደን ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሄትሮ ወደ ሚገኘው የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ካቀኑ ሠራተኞች መካከል ነበረች።
"ይህ ለኔ በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነው። እጅግ በጣም ተበሳጭቻለሁ።" ብላለች።
የዚህ ሁሉ ጣጣ መንስዔ ኮሮናቫይረስ ነው።
ብሪቲሽ ኤርዌይስ ልክ እንደ ሌሎች አየር መንገዶች ሁሉ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የምጣኔ ሃብት ድቀት ደርሶበታል። እስከ ባለፈው ሰኔ ድረስ ብቻ የ700 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራ ደርሶበታል።
በተለይ እንግሊዝና አውሮፓ የእንቅስቃሴ ገደብ በጣሉበት ወቅት ለሳምንታት ያክል በቀን በጣት ከሚቆጠሩ በረራዎች በላይ ማከናወን አልቻለም።
ኩባንያው የበረራ ኢንዱስትሪ እስከ ፈረንጆቹ 2023 ድረስ አያገግምም ይላል።
አየር መንገዱ ባለፈው ሚያዚያ ነው ሠራተኞችን ሊቀንስ እንደሚችልና የማይቀነሱ ሠራተኞች ደግሞ ደመወዛቸው እንደሚቆርጥ ይፋ ያደረገው።
ኩባንያው ከሠራተኞች ማሕበራት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ዕቅዱን እንደሚገፋበት አስታውቆ ነበር። ይህን የሚያደርገውም ለሠራተኞች ቁርጣቸውን የሚያሳውቅ ደብዳቤ በመበተን መሆኑን ተናግሯል።
የሠራተኞ ማሕበራት ይህ የአየር መንገዱ ውሳኔ አስቆጥቷቸዋል።
በርካታ የሕዝብ እንደራሴዎችም የአየር መንገዱን ውሳኔ ሲተቹ ነበር። ወግ አጥባቂው ሃው ሜሪማን 'ይህ ግንባር ላይ ሽጉጥ እንደመደገን ነው' ሲሉ ተደምጠዋል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ የአየር መንገዱን ሠራተኞች በሚወክሉ ማሕበራትና በአየር መንገዱ መካከል ስምምነት አልተደረሰም። አየር መንገዱ ደግሞ በዕቅዴ መሠረት ደብዳቤ ልበትን ነው እያለ ነው።
ጆን [ስሙ የተቀየረ] በ50ዎቹ ዕድሜው የሚገኝ ለብሪቲሽ ኤርዌይስ የሚያገልግል ኢንጂነር ነው። የጆን ጭንቀት ደግሞ ከተባረርኩ እንደ እኔ ዕድሜው የገፋ ሰውን የሚቀጥር ሌላ ድርጅት የለም የሚለው ነው።
ጆንም ሆነ ቪኪ ቁርጣቸውን ዛሬ ያውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። አየር መንገዱ በዕቅዴ መሠረት እገፋበታለሁ ይበል እንጂ የሠራተኛ ማህበራት ደግሞ እርምጃ እንወስዳለን በማለት እየዛቱ ነው።