ዶናልድ ትራምፕ 'ቲክቶክ' አሜሪካ ውስጥ እንዳይሰራ ሊያግዱ ነው

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከወደ ቻይና መጥቶ ዓለምን ጉድ እያሰኘ የሚገኘው 'ቲክቶክ' የተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ አሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል እንደሚያግዱት አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ''እስከ ቅዳሜ ድረስ ባለው ጊዜ ውሳኔውን ማስተላለፍ እችላለሁ'' ብለዋል። 'ባይትዳንስ' በመባል በሚታወቀው የቻይና ድርጅት የሚተዳደረው ቲክቶክ የአሜሪካውያንን ግላዊ መረጃ ለመበርበር ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል የአሜሪካ የደኅንንት ኃላፊዎች ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

ቲክቶከ በበኩሉ ከቻይና መንግሥት ጋር መረጃ ይለዋወጣል መባሉን አስተባብሏል።

በዓለም ላይ በፍጥነት ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣው ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ እስከ 80 ሚሊየን የሚደርሱ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን እገዳው ለድርጅቱ ትልቅ ኪሳራ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

''ቲክቶክን በተመለከተ፤ አሜሪካ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እናግዳቸዋለን'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ኤር ፎርስ ዋን ወደ ሚባለው አውሮፕላናቸው ውስጥ እየገቡ።

የቲክቶክ ቃል አቀባይ ሂላሪ ማክኩዌድ ከዋሽንግተን ፖስት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በውሳኔው ላይ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፤ ድርጅቱ ግን አሁንም ቢሆን የረዥም ጊዜ የስኬት እቅዱ እንደማይጎዳ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቲክቶክን ለመዝጋት ምን አይነት ስልጣን እንደሚጠቀሙ፣ እገዳው እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን እና ምን አይነት የሕግ መሰናክሎች እንደሚጠብቃቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ማይክሮሶፍት ደግሞ በቅርቡ ቲክ ቶክን ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው ለባለቤቱ ባይትዳንስ ያሳወቀ ቢሆንም የፕሬዝዳንቱ ንግግር ምን አይነት ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችልም እስካሁን አልታወቀም።

ቲክቶክን በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ ያሰተላላፉት መልእክት በዋሽንግተን እና በቤይጂን መካካል እየተካረረ የመጣው አለመግባባት ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ገምተዋል።

አሜሪካ እና ቻይና በንግዱ ዘርፍ ከነበራቸው አለመግባባት ባለፈ ከኮሮናቫይረስ በኋላ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያም ሲወነጃጀሉ ቆይተዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ባይትዳንስ በቲክቶክ በኩል የሚሰበስበውን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል በማለት ሲወነጅሉ ቆይተዋል።

ቲክቶክ ሁሉም የአሜሪካ ተጠቃሚዎቹን መረጃ እዚያው አሜሪካ ውስጥ እንደሚያስቀምጥና መጠባበቂያው ደግሞ ሲንጋፖር ውስጥ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ አስታውቋል።

በዚህ ሳምንት ደግሞ ለተጠቃሚዎቹ እና ለተቆጣጣሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት የመተግበሪያውን አሰራር መመልከት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ከፍተኛ ግልጽነት ያለው ሂደት እንደሚከተል ገልጿል።

''ዓላማችን ፖለቲካዊ አይደለም፣ ማንኛውም አይነት ፖለቲካዊ ማስታወቂያም ሆነ አጀንዳ ይዘን አናቀርብም፤ የእኛ ዋነኛ አላማችን ፈጠራን በማበረታታት ተጠቃሚዎቻችን እንዲዝናኑ ማድረግ ብቻ ነው'' ብለዋል የቲክቶክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬቨን ሜየር።

አክለውም ''ቲክቶክ አዲሱ የአሜሪካ ኢላማ ሆኗል፤ ነገር ግን እኛ ጠላት አይደለንም'' ብለዋል።