ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እምነቱን በማዋረድ የተከሰሰው ፓኪስታናዊ ፍርድ ቤት ውስጥ በአንድ ግለሰብ በጥይት ተገደለ
እምነትን በማዋረድ ችሎት ፊት ቀርቦ የነበረው ፓኪስታናዊ በፍርድ ቤቱ ውስጥ በአንድ ግለሰብ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አልፏል። ግለሰቡ በሰሜናዊ ፓኪስታን በምትገኘው ፔሽዋር የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል ነበር የተተኮሰበት።
ታሂር አህመድ ናሲም የተባለው ይህ ግለሰብ ነብይ ነኝ ብሏል በሚል ነበር ክስ የተመሰረተበት፤ በዚህም ሁኔታ እምነቱን ዝቅ አድርጓል ተብሏል።
ሃይማኖትን መሳደብ፣ ወይም ማዋረድ በህጉ መሰረት የሞት ቅጣት የሚያስፈርድ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ይሄ ተግባራዊ የሆነበት ሰው የለም። ነገር ግን እምነታቸውን አዋርደዋል ተብለው የተወነጀሉ ሰዎች ክፉኛ ጥቃት ይድርስባቸዋል።
ታሂር ክሱ የተመሰረተበት ከሁለት አመት በፊት አንድ ታዳጊ እምነቱን አዋርዷል ብሎ መወንጀሉን ተከትሎ ነው።
በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት በጥይት ሲተኮስበት ተዝለፍልፎ ወንበሩ ላይ እንደወደቀም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣው ቪዲዮ ያሳያል።
ታሂርን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ እዚያው እጅ ከፍንጅ ተይዟል። በወቅቱም በእጅ ሰንሰለት ታስሮ ታሂርን "የእስላም ጠላት" እያለም ሲጮህ ታይቷል።
ታሂር ናሲም እምነቱን በመስደብ የተከሰሰው አዋይስ ማሊክ የሚባል የእስልምና እምነት ተማሪ ነበር።
በወቅቱ በአሜሪካ ይኖር የነበረው ታሂር፣ ከአዋይስ ጋር በኢንተርኔት ስለ እምነት አውርተው ነበር። ወደ ፓኪስታንም ከመጣ በኋላ አንድ የመገበያያ መደብር ውስጥ አግኝቶት ስለ እምነቱ ያለውን አስተያየት በመጠየቅ ታሂር የሚለውን ሰምቶ ለፖሊስ ማሳወቁንም ይሄው ታዳጊ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ታዳጊው ፍርድ ቤት እንዳልቀረበና ስለ ተኩሱም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሯል። ታሂርን በመግደል የተጠረጠረው ካሊድ ሽጉጥ ወደ ፍርድ ቤቱ ማስገባት እንዴት እንደቻለ የተባለ ነገር የለም።
ታሂር መናፍቃን ተብለው ከሚወነጀሉት የአህማዲ ቡድን ተከታይ የነበረ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረው፣ ነገር ግን ከጊዜያት በኋላ ይህንን ትቶ ራሱን ነብይ ብሎም ይጠራ ነበር ብለዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ መሪ እንዲሁ ታሂር የአዕምሮ ህመምተኛ እንደነበርና ራሱንም የአምላክ መልዕክተኛ ነኝ በማለት በዩቲዩብ የቪዲዮዎች መልእክት ያስተላልፍ ነበር ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ፓኪስታን እምነትን በመስደብ ያላት ህግ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ አናሳ ማህበራት ላይ ያነጣጠረና ለደቦ ጥቃትም በር የሚከፍት ነው ይላሉ። በርካታ ፓኪስታናውያንም እምነታቸውን አዋርደዋል በሚል በተቆጡ ቡድኖች እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል።