ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ባለሥልጣኗ ‘ወንበዴ’ ስለመባላቸው ከዚምባብዌ አምባሳደር ማብራሪያ ጠየቀች
አሜሪካ በዚምባብዌ ባለሥልጣን ስለተሰጠው አስተያየት የአገሪቱ አምባሳደር ማብራሪያ እንዲያቅርቡ ጠይቃለች።
አሜሪካ ዚምባብዌ ውስጥ የምታካሂደውን ምርመራ በተመለከተ ትችት አዘል አስተያየት ተሰንዝሮ ነበር።
የዚምባብዌ ገዢ ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ ቃል አቀባይ፤ “አሜሪካ ጸረ መንግሥት ንቅናቄ ትደግፋለች” ብለው ሰኞ እለት ከሰው ነበር።
የአሜሪካው አምባሳደር ብራየን ኒኮላስን ‘ወንበዴ’ ብለው ዘልፈውም ነበር።
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ተባባሪ ጸሐፊ ቲቦር ናጊ፤ የተባለው ነገር “በጣም አስጸያፊ ነው” ብለዋል።
የአሜሪካ ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ ጂም ሪች፤ ዚምባብዌ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና ባለሥልጣኖችን በመዝለፍ የምጣኔ ሀብት እና የፖለቲካ ቀውሷን ለመሸፈን እየሞከረች ነው ብለዋል።
የአሜሪካው አምባሳደር ብራየን ኒኮላስ ከዚምባብዌ መንግሥት ጋር ሲጋጩ የመጀመሪያቸው አይደለም።
የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አምና አምባሳደሩን ለማባበበር ሲዝት እንደነበር ይታወሳል። አምባሳደሩን “እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል እየሆኑ ነው” በሚልም ወንጅሏቸዋል።
ዚምባብዌ በአሜሪካ የተጣሉባትን ማዕቀቦች በጥብቅ ትቃወማለች።
ባለፈው ሳምንት ዛኑ ፒኤፍ በአገሪቱ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ድጋፍ በማድረግ የአሜሪካ ኤምባሲን መወንጀሉ አይዘነጋም።
አምባሳደሩን ከአገር አባርራለሁ በማለትም አስፈራርቷል።
ተቃውሞ በአገሪቱ የተስፋፋው ሙስናን ለመቃውም ነው ቢባልም፤ የፓርቲው ቃለ አቀባይ ፓትሪክ ቺናማሳ መንግሥትን ለመገልበጥ የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።
ተቃዋሚዎቹ በዚህ ተግባራቸው የሚቀጥሉ ከሆነም ተመጣጣኝ ኃይል መንግሥት እንደሚጠቀምም አስጠንቅዋዋል።