አሜሪካ የኮቪድ-19 ክትባት ምርምሮችን ‘ሰልለዋል’ ያለቻቸውን ቻይናውያን ከሰሰች

ቻይና የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር የሚያካሂዱ ቤተ ሙከራዎች ላይ ስለላ እያደረገች ነው ሲል የአሜሪካ የፍትህ ተቋም ወነጀለ።

በኮሮናቫይረስ ላይ የሚደረግ ምርምርን ሰልለዋል የተባሉ ሁለት ቻይናውያን ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ክሱ የተመሰረተው አሜሪካ ቻይናን በበይነ መረብ ስለላ አምርራ መተቸቷን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ፤ ሩስያ የኮቪድ-19 ምርምር ለመስረቅ ሞክራለች ብለው ነበር።

አሜሪካ የከሰሰቻቸው ቻይናውያን የቀድሞ የኤሌክትሪክ ምህንድስና ተማሪዎቹ ሊ ዢያዩ እና ዶንግ ጂአዚ ናቸው። የንግድ ሚስጥር በመስረቅና ለበይነ መረብ የገንዘብ ምዝበራ በመመሳጠር ተወንጅለዋል።

ክሱ ምንድን ነው?

ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ከሆነ ሁለቱ ቻይናውያን መጋቢት ላይ የማስቹሴትስ የባዮቴክኖሎጂ ተቋምን ሰልለዋል። በተቋሙ ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ጥናት እየተደረገ ይገኛል።

ሜሪላንድ የሚገኝ ድርጅት ኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን አስታውቆ በሳምንቱ ቻይናውያኑ የድርጅቱን በይነ መረብ ሰርስረው እንደገቡም ተገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ በግላቸው በበይነ መረብ መረጃ ቢሰርቁም፤ አልፎ አልፎ የቻይና ሰላዮች ድጋፍ ያደርጉላቸዋል ተብሏል። ድጋፍ አድርገዋል ከተባሉት መካከል የቻይና የብሔራዊ ደህንነት ኃላፊ ይገኙበታል።

ከጎርጎሮሳውያኑ 2009 ወዲህ በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ ሚስጥር እና አዕምሯዊ ንብረት መስረቃቸውን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ቻይና የሚኖሩት እነዚህ ግለሰቦች፤ ስለ ኮሮናቫይረስ ክትባት፣ ህክምና እና ምርመራ መረጃ ለማግኘት የባዮቴክ ተቋማትን የመረጃ መረብ ደህንነት ጥሰዋል።

ከአሜሪካ በተጨማሪ አውስትራሊያ፣ ቤልጄም፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ሊቱኒያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስፔን፣ ስዊድን እና ዩናይትድ ኪንግደም ኢላማ ተድገዋል።

ቻይናውያኑ የዩኬን ሰው ሰራሽ ክህሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ተቋም፣ የስፔንን የመከላከያ ተቋም እና አውስትራሊያን የፀሐይ ብርሃን ሀይል ተቋም ሰረስረው መግባታቸው በክሱ ተመልከቷል።

ቻይና ለምን ስለላውን ትደግፋቸዋለች ተባለ?

ዐቃቤ ሕግ እንደሚናገረው፤ ግለሰቦቹ ለግል ጥቅማቸው የሚሠሩበት ጊዜ አለ። ከዚህ በፊት አንድ ድርጅት ሚስጥሩን እንዳያጋልጡበት ገንዘብ እንዲከፍላቸው መጠየቃቸው እንደ ምሳሌ ተጠቅሷል።

ከግል ጥቅም ባሻገር ግን ለቻይና መንግሥትም ያገለግሉ ነበር ተብሏል።

ወታደራዊ መረጃ ሰርቀው ለቻይና መንግሥት መስጠታቸው በክሱ ተገልጿል።

በተጨማሪም የሆንግ ኮንግ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ እንዲሁም የቀድሞ የቲያናመን አደባባይ ተቃዋሚን የይለፍ ቃል ለቻይና መንግሥት አሳልፈው ሰጥተዋል ተብሏል።

ተባባሪ ዐቃቤ ሕግ ጆን ደምረስ “ቻይና ለበይነ መረብ ወንጀለኞች ከለላ በመስጠት አሳፋሪ የሆኑትን የሩስያ፣ የኢራን እና የሰሜን ኮርያን ጎራ ተቀላቅላለች። ግለሰቦቹ በድካም ያገኘነውን አዕምሯዊ ንብረት ለቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ያስተላልፋሉ” ብልዋል።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንያንግ፤ ቻይና አሜሪካ ላይ የበይነ መረብ ጥቃት ከፍታለች የሚለውን ክስ አጣጥለዋል። ኮቪድ-19ን የተመለከቱ ምርምሮችን ለመስረቅ ተሞክሯል የሚለውን ውንጀላም “የማይመስል” ሲሉ አስተባብለዋል።

በያዝነው ወር መባቻ የአሜሪካ የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ዋሪ፤ ቻይናን “የዓለም ብቸኛዋ ፈርጣማ አገር ለመሆን የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም” ማለታቸው ይታወሳል።

ድርጅቱ አሁን ላይ በየአስር ሰዓቱ ከቻይና ጋር የተያያዙ የደህንት ሥራዎች እንደሚያከናውን ተናግረዋል። በተቋሙ ሥር ካሉት ወደ 5,000 የሚጠጉ የደህንነት ጥበቃ የምላሽ ስለላዎች (ካውንተርኢንተለጀንስ) መካከል ግማሹ ቻይና ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውንም አክለዋል።