ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአርሶ አደሮችን ተስፋ ያሳካ ይሆን?
ጂፋሬ ግርማ አርባ ሁለት ዓመቷ ነው። ስምንት ልጆች አሏት። ሁሉም ልጆቿ አብረዋት ይኖራሉ። ትልቁ ሃያ ሁለት ዓመቱ ሲሆን የሙያ ስልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛል። ሌሎችም ልጆች እንደዚሁ ተማሪ ናቸው።
የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝን ተከትሎ በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት አሁን ሁሉም ልጆች ከመደበኛ ትምህርት ተራርቀዋል። እርግጥ ቤት ውስጥ ሲኖሩ ቤተሰባቸውን ሥራ ያግዛሉ፤ ከብቶችን ያግዳሉ፤ ኩሽና ውስጥ ምግብ በማብሰልም የሚችሉትን ይሰራሉ።
የጅፋሬ ኩሽና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ሚሊዮን የአርሶ አደር ቤተሰብ ማዕድ ቤቶች ብዙም የተለየ አይደለም። ከሳር የተበጀ ጣራ፣ ከጭቃ እና እንጨት የተሰራ ግድግዳ፣ እፍንፍን ያለ ክፍል።
ሁለት በመጠን የተለያዩ ምድጃዎች ከእነሸክላ ጉልቻዎቻቸው ራቅ ራቅ ብለው አሉ፤ አንደኛው የእንጀራ መጋገሪያ ሲሆን ሌላኛው አነስ ያለ ለወጥ እና የመሳሰሉ ነገሮች መስሪያነት ያገለግላል። የኩሽናው ወለል ለወትሮው በእበት የሚለቀለቅ ቢሆንም ቢቢሲ በወርሃ ሐምሌ ቤቷ በተገኘ ጊዜ በክረምቱ ምክንያት ጨቅይቶ ነበር። ከኩሽናው ጋር በር በሚጋራ ክፍል ውስጥ ላሞች ይታለባሉ።
ጂፋሬ ከአዲስ አበባ ብዙም በማትርቅ፤ ከእንጦጦ ተራራ ከአስር የማይበልጥ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ አካኮ በምትሰኝ መንደር ውስጥ ትኖራለች።
መንደሪቷን የከበበውን ጫካ አቆራርጠው ትንሽ ከተጓዙ አመሻሽ ላይ መዲናይቱን ያጥለቀለቃት የኤሌክትሪክ ብርሃን ውቅያኖስ ሲንቦገቦግ ማስተዋል ይቻላል።
የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ላይ ከተንቸረፈፈው የኤሌክትሪክ ኃይል ለአካኮ እንጥፍጣፊ አልደረሳትም።
ጭስ፣ ጥላሸት፣ አመድ
ጂፋሬ ምግብ የምታበስለው፣ እንጀራ የምትጋግር ዳቦ የምትደፋው፣ ወጥ የምትወጠውጥው፣ ቡና የምታፈላው በአስር ሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን መሰሎቿ የኤሌክትሪክ ኃይል በሚሰጠው ምቾት፣ ቅልጥፍናና ሥራን የማቃለል ፀጋን በሚያላብሰው የአሌክትሪክ ኃይል ታግዛ አይደለም።
ሁሉንም ነገር የምንሰራው በእንጨት ማገዶ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ከሰልም የቡታጋዝ (ኬሮሲን ምድጃ) እንጠቀማለን" ለቢቢሲ ብላለች። ኩሽና ውስጥ ከእንጨት ማገዶ ጋር መርመጥመጥ ፈታኝ ነገር ነውም ትላለች ጨምራ።
"ሰውነታችን አመድ ይለብሳል፤ ጭሱ አሰከረን፤ ጥላሸቱን እንከናነባለን" በማለት ኩሽና ውስጥ የዕለት ከዕለት ገጠመኝ በአጭሩ ትገልጸዋልች።
ለማገዶነት የሚውለው እንጨት በአካባቢው ካለው ጫካ የሚለቀም ሲሆን ይሄንን ማድረጉ "በጣም አድካሚ ነው" እንደ ጂፋሬ።
ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ አካኮ መንደር የሚያቀና ተጓዥ በመንገዱ ዳርና ዳር ጉልበታቸውን እየተፈታተነ እንደሆነ አካላዊ ገፅታቸው የሚመስክርለትን ትልልቅ የማገዶ እንጨት ክምር የተሸከሙ ሴቶችን መመልከት ብርቅ አይሆንበትም።
ብዙዎቹ የማገዶ እንጨቱን ሸጦ ጥቂት ገንዘብ ለማግኘት በሚመስል ምክንያት ወደ መዲናዋ ሸክሙን ይዘው ሲጓዙ ይስተዋላል። አንዳንዶቹ እንጨቱን ለግላቸው የማገዶ መጠቀሚያነት ወደ መንደራቸው ይዘው የሚሄዱ እናቶችና ወጣት ሴቶችም ማየት ይቻላል።
ጂፋሬ እና ጎረቤቶቿ ወደቀያቸው የኤሌክትሪክ ኃይል በበቂ ሁኔታ ይዳረሳል ተብሎ ቃል ሲገባ ቢሰሙም ፍሬ ያለው ነገር ያለማስተዋላቸውን ለቢቢሲ ይናገራሉ።
የኤሌክትሪክ ኃይል ቢገባ "ንፁህ እንሆናለን፤ ልብሳችን ይነፃል፤ በፍጥነት እንሰራለን፤ ሁሉ ነገራችን ይሻሻላል" ትላለች ጂፋሬ ለኤሌክትሪክ ኃይል እሷና ጎረቤቶቿ ያላቸውን ምኞችት ስትገልጽ።
አስተዋጽኦ ለግድቡ ግንባታ
ባለቤቷ ለማ ሹሚ ትንሽ ማሳው ላይ ገብስ ያበቅላል። ከዚህም በተረፈ ከብቶች ስላሉት እነርሱን ያረባል። ቤተሰቡን የሚደጉምበት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትም መቀመጫውን ከመንደሪቷ መንደር ተጠግቶ ባደረገ አንድ የምርምር ተቋም በትርፍ ሰዐት በጥበቃነት ተቀጥሮ ይሰራል።
ቢቢሲ ቤቱ በተገኘበት ማለዳ የእረፍት ቀኑ ስለነበር ቤት ውስጥ ተቀምጦ ከዘመዶችና ጎረቤቶቹ ጋር ይጨዋወት ነበር። አልፎ አልፎ በቅርብ ባለው መስክ ላይ ከብቶችን የሚያግድ አንደኛውን ልጁን ወጣ እያለ ያያል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለበርካቶች የኤሌክትሪክ ብርሃንን በማዳረስ፤ እያደገ ላለው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት እየጨመረ የሚሄድ የኃይል ፍላጎትም ጥሩ መላ ይሆነኛል ብሎ ከጠኝ ዓመት በፊት የጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የለማን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያገኘ ነው።
ለዚህም ለማ በጥበቃ ሥራ በሚያገለግልበት የምርምር ተቋም በኩል ከወርሃዊ ደምወዙ የሚቀነስ መዋጮ ከማድረጉም በዘለለ፤ መንግሥት ያቀረበውን ቦንድም ገዝቷል።
"የሦስት መቶ ብር ነው የገዛሁት፤ ያው ባ'ቅማችን ልክ" ሲል ለግድቡ ያበረከተውን አስተዋጽኦ እየሳቀ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ገንዘቡ አምስት ዓመቱን ጠብቆ እንደተመለሰለትም ይናገራል።
ከዚህም ባለፈ ከቀጣሪ መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር በመሆን ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት የእኔ የሚለውን ግድብ በቦታው ተገኝቶ መጎብኘቱንም ይናገራል።
"መቼም. . . እዚህ መድረሱ ተመስገን ነው" ይላል ከግድቡ ውሃ ለመሞላት መቃረብ ጋር በተያያዘ አስተያየቱን ሲጠየቅ።
ለማ ግድቡ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ለመንደሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ይዳረሳል የሚል እምነቱ ከወትሮውም የበለጠ የጨመረ ይመስላል፤ "ተስፋችን ብዙ ነው።"
የአርሶ አደሩ ተስፋና ድርድሩ
ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ ከ65 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው እንደ ጂፋሬ ግርማና ባለቤቷ ለማ ሹሚ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሩቅ ህልም ነው። በዚህም ለዕለት ከዕለት የኃይል ፍልጎታቸው በርካታ እናቶችና ህጻናት የማገዶ እንጨት በመሰብሰብ በየቦታው መባዘን የዘወትር ህይወታቸው አካል ነው።
ከዚህ ባሻገርም ምግብ ለማብሰልና ለብርሃን ጥቅም ላይ በሚውሉት ማገዶዎች የተነሳ ለተለያዩ ከባድ የጤና ችግሮች ይጋለጣሉ። በተጨማሪም በሴቶችና በታዳጊዎች የወደፊት ህይወት ላይም ከባድ ተጽእኖን ያሳርፋል።
ግብጽና ሱዳን ግድቡ ለዘመናት የሕዝባቸው ህይወት መሰረት የሆነውን የአባይ ወንዝ ውሃ መጠን ይቀንስብናል በማለት በተፈጠረባቸው ስጋት እስካሁን በተደረጉት ድርድሮች ከስምምነት ላይ ባይደረስም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የገጠሩን ህዝብ ህይወት ለመቀየርና ምጣኔ ሃብቱ የሚፈልገውን ኃይል ለማቅረብ ግድቡን ሥራ ከማስጀመር ውጪ አማራጭ እንደሌለ እየገለጸ ነው።
የኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ ከታሰበበት ጊዜ የዘገየ ቢሆንም አሁን የግንባታው ከሦስት አራተኛው በላይ መጠናቀቁ የተነገረለት ሲሆን በቀጣይ ዓመት የመጀመሪያ ደረጃ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።
አርሶ አደሩ ለማ ሹሚ ከሚያገኟት ትንሽዬ ወርሃዊ ገቢ አንስቶ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለግንባተው አስተዋጽኦ ያደረገበት ይህ በአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የተነገረለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ያመነጫል።
ወደ አምሰት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይደረግበትል ተብሎ የሚታሰበው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አብዛኛው በገጠር ነዋሪ ከሆነው ሕዝቧ መካከል በርከት ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋዳሽ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ባሻገርም ለበርካታ ሕዝቧ የሥራ ዕድልን ለሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ግብአት የሆነውን ኃይል ከማቅረቡ ባሻገርም አሁን በውስን ደረጃ ለጎረቤቶቿ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ መጠን ይጨምረዋል ተብሎ ይታመናል።
ወይዘሮ ጂፋሬና ባለቤቷ አቶ ለማ የግድቡ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ ተስፋ የሰጣቸው ቢሆንም በወንዙ ውሃ ላይ የሚገባን ጥቅም ይከበር ከሚሉት ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የሚደረገው ድርድር ገና መቋጫ አላገኘም።
ቀድሞውንም ከስምነት ተደረሰም አልተደረሰ ግድቡን የውሃ ሙሌት እንደምትጀምር አስታውቃ የነበረችው ኢትዮጵያ የግንባታ ሥራዋን እያፋጠነችው እንደሆነ ይነገራል። በክረምቱ ምክንያት የሚጥለው ከፍተኛ የዝናብ መጠንም ለግድቡ ውሃ ማቀቢያነት በተዘጋጀው ቦታ ላይ መጠራቀም መጀመሩን የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል።
በአገራቱ መካከል በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ሲካሄድ ቆይቶ ያለስምምነት የተጠናቀቀው ድርድር የተነሱ ጉዳዮችን በመመርመር ቀጣይ እርምጃዎችን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።