ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ በባለሙያ እይታ
ከህዳሴ ግድቡ አካባቢ የተገኙ ሳተላይት ምስሎች የግድቡ የውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን ያሳያሉ፤ በርካቶች ግድቡ ውሃ መሞላት ጀምሯል ሲሉ ጥያቄ ቢያቀርቡም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ግን በይፋ የተጀመረ ነገር የለም ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አዲሱ የሳተላይት ምስል የተወሰደው ሰኔ 20/2012 እና ሐምሌ 5/2012 ሲሆን ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን በተከታታይ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል። የግድቡ ውሃ መጨመርንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በውሃ ፖለቲካ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላቸው አነጋግረናቸዋል።
ግድቡ ውሃ መያዙን ማረጋገጣችንን ተከትሎ ከግብጽ በኩል የተለየ ምላሽ መጠበቅ እንችላለን?
ምንም የተለየ ምላሽ አይኖርም። ያው ሌላ ጊዜም እንደሚሉት ማስፈራራት የተለመደው ካልሆነ በስተቀር ምንም ማድረግ አይኖርም። ያው በአረብ አገራት በኩል ጫና ሊያሳድሩብን ይሞክሩ ይሆናል። ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ግጭቶችን በማባባስ ወደዚያ ውጥረት ሊያስገቡን ይሞክሩ ይሆናል። አገር ውስጥ ያሉትን አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ደግሞ አሁን ያለውን ሁናቴ ተጠቅመው እርስ በእርሳችን ማተራመስ ይፈልጉ ይሆናል። ከዚያ በተረፈ ግን በቀጥታ ጥቃት የሚባል ነገር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም። እርሱ በተግባር ሲታይ የማይቻል ነው።
ኢትዮጵያና ግብጽ ግን ግድቡን በተመለከተ ስምምነት ለይ መድረስ አይችሉም?
አሁን የሚያጣላው ነገር እኮ ግድብ ውሃ መሙላቱ አይደለም። ከተሞላ በኋላ የሚለቀቀው ውሃ ነው ትልቁ ችግር። እነርሱ የሚፈልጉት ከተሞላ በኋላ የሚለቀቀው ውሃ መጠኑን አሁኑኑ እንወቀው ነው። እኛ ደግሞ ይህንን ግድብ ብቻ አይደለም የምንሰራው ከግድቡ በላይ ሌሎች ወደ ፊት ለምንሰራቸው ፕሮጀክቶች ውሃ ሲያስፈልገን መጠቀም አለብን ስለምንል አሁኑኑ ይህን ያህል ውሃ እንለቅላችኋለን ብለን ቃል መግባት የለብንም ነው። ለነገሩ እርሱ የኛ የሱዳንና የግብጽ ጉዳይም አይደለም። የ11 የተፋሰስ አገራት ጉዳይ ስለሆነ ብቻችንም የሚለቀቀው ውሃ ላይም መስማማት አይገባንም።
ሌሎቹ የተፋሰሱ አገራት ከጎናችን የቆሙትም ማግለልና ማስቀየም ስለሚሆንብን እርሱንም አሁን ቃል መግባት የለብንም። ድርቅ ሲኖር የሚለቀቀው የሚሉት ጉዳይም እርሱም ለሚፈጠረው ድርቅ እኛ ኃላፊነት አንወስድም። ለነገሩ ድርቅ የሚፈጠረው ኢትዮጵያ ውስጥ እንጂ እነርሱ ጋር አይደለም። ስለዚህ ድርቅ በተፈጠረ ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀንሰው ውሃ የእነሱን ውሃ ለማካካሻ እንድናደርገው ነው የሚፈልጉት። እርሱ ራሱ ነው እንጂ የሚያጣላን መሙላቱ አይደለም። ከአራት እስከ ሰባት አመት መሙላቱም አይደለም የሚያጣላን። ከተሞላ በኋላ ያለው የውሃ አለቃቀቅ ነው የሚያጣላን። እርሱ ደግሞ ከብሔራዊ ጥቅማችን አንጻር ልናደርገው የምንችለው አይደለም። ወደፊት በአባይ ወንዝ ላይ ያለንን ነገር ሁሉ የሚገድብ ነገር ስለሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በጎርጎሳውያኑ 1959 የፈረሙትን፣ ብቻችንን እንጠቀማለን የሚሉትን፣ እውቅና መስጠት ነው የሚሆነው እና ኢትዮጵያ ወደዚህ መግባት አትፈልግም አሁን።
ኢትዮጵያግድቡን መሙላት መጀመሯ ግብጽ እንድትለሳለስ ያደርጋል ብለው ያስባሉ?
አዎ። የዘንድሮው ውሃ መሙላት ምንም ማለት አይደለም። አንደኛ 4.9 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ነው የምንሞላው። ይህ ደግሞ ከአባይ ዓመታዊ ፍሰት አንድ አስረኛው ነው። ይህ ማለት ደግሞ ዘንድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንጀምራለን ማለት አይደለም። ምክንያቱም የሚቀጥለው ዓመት የምንጠብቀው ሌላ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አለ። የሁለቱ ድምር ውጤት ነው የኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም የሚፈጥርልን። እና እኛ አሁን የምናደርገው ያለው በሚቀጥለው አመት ብዙ ውሃ ከምናስቀርባቸው ትንሽ ትንሽ በማድረግ በሁለት ዓመት ከፍለነው ነው። እነርሱን የሚጠቅም ነው።
ሁለተኛ ግብጾች አሁን የሚቸግራቸው ለህዝባቸው የገቡት ቃል ነው። እኛ ታሪካዊ መብት አለን፣ ይህ ግድብ እኛ ስልጣን ላይ እያለን አይሞላም በሚል የገቡት ቃል ነው የሚያስቸግራቸው። እንዳውም ግድቡ ውሃ መሞላቱን በአደባባይ እንዲነገር የሚፈልጉት አይመስለኝም። ምክንያቱም ግድቡን እስኪሞሉት ድረስ ምን ትሰሩ ነበረ የሚል ጥያቄ ሕዝቡ ያነሳባቸዋል። እናም እነርሱ ፊት ለፊት እያሳወቁ ባይሆን ዘንድሮ የሚያዘው ውሃ ብዙ የሚጎዳን አይደለም እያሉ ሕዝባቸውን ቢያረጋጉ ነው የሚሻላቸው። መሙላታችን የማይቀር ስለሆነ እነርሱንም ችግር ውስጥ እንዳያስገባቸው የሚሞላው ውሃ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ አይደለም በማለት ሕዝባቸውን ማረጋጋት እና ይህንን መቀበል ነው የሚያዋጣቸው።
በዚህ በሁለቱ አገራት ድርድር መካከል የሱዳን ሚና እየተረሳ መጥቷል የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ፤ ሱዳን ትልቅ ሚና እንዳላት ብዙዎቹ ስለሚያምኑ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ድሮም ቢሆን ግብጾች የሚሞክሯቸው ነገሮች ነበሩ። ዋናው የውሃ ተጠቃሚ ግብጽ ናት። ዋናው ውሃ አመንጪ አትዮጵያ ናት።እና ትልቁ ጉዳይ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ስለሆነ ያለው እናንተ መካከል ላይ ሆናችሁ አደራድሩን ነው የሚሏቸው። እርሱ አደገኛ ጉዳይ ነው። እንደ ባለጉዳይ ያለማየት ነገር ነው። በአባይ ተፋሰስ ሱዳን አይደለችም ሩዋንዳም፣ ብሩንዲም፣ አስራ አንዱም አገራት ባለጉዳይ ናቸው። ስለዚህ ሱዳን ተመልካች የምትሆንበት ጉዳይ የለም። እነርሱም አይቀበሉትም። ምንድን ነው አሁን ሱዳን ውስጥ ያለው የጥምር መንግሥት ስለሆነ ያለው፣አንድ አይነት አቋም ስለማይዝ የተደላደለ እና በሁለት እግሩ የቆመ መንግሥት ስላልሆነ፣ እዚህ መንግሥት ላይ ደግሞ ጫና መፍጠር ስለሚችሉ እርሱን እያገለሉ መቀጠል ይፈልጋሉ። ግን ሱዳን አደራዳሪ መሆን አትፈልግም፤ መሆንም አይገባትም። ግን የቆየ ፍላጎት ነው። ግብጾች በተደጋጋሚ ሲሞክሩት የነበረው ነው።
በተናጠል ከኢትዮጵያ ጋር ለመገናኘት ሲሞክሩ ኢትዮጵያ አይሆንም እያለች የቆየችው ነገር ነውና ሱዳን ባለጉዳይ ናት። ኢትዮጵያና ሱዳን አንድ አይነት አቋም የሚይዙ ከሆነ ይጠነክሩብናል ስለሚሉ ነው ለመከፋፈል እንደተደራዳሪ ሳይሆን እንደ አደራዳሪ ሊያይዋት የሚፈልጉት።
ግብጽም ሆነ ኢትዮጵያ የራሳቸው የሆነ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አላቸው። ግብጽ ሊቢያ ድረስ በመሄድ ከቱርክ ጋር ግጭት ውስጥ እንዳለች ይሰማል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለግብጽ እንደ እድል ሊቆጠር የሚችል ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ማሰባቸው አይቀርም። ለነገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ጀርባ ሁል ጊዜ ግብጾች እጃቸው አለበት። የኤርትራ ነጻ አውጪ መመስረት ላይ፣ ከድሮ ጀምሮ ከ1950ዎቹ፣ 60ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥቱ ነዋይ ወቅት የነበረው መፈንቅለ መንግሥት ላይ ወታደር እስከ መላክ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አለመረጋጋት ሁሉ እጃቸው እንዳለበት እሙን ነው።
እኛ የአገራችንን ጉዳይ በአገራችን መፍታት ነው። የውስጣችን ጉዳይ የውስጥ ነው፤ እኛው ራሳችን መፍታት አለብን። ለእነርሱ ግን መግቢያ ቀዳዳ መፍጠር የለብንም። እና ይህንን ለመጠቀም መፈለጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በተለያየ መንገድም ይሞክሩታል። . . .የራሳችን ችግር በራሳችን ከፈታን የእነርሱ ተላላኪ የሚሆን ኃይል ማሳጣት ይቻላልና በውስጣችን ያለውን ነገር ነው መስራት ያለብን። አላስፈላጊ ጉዳዮችን እየመዘዝን፣ እርሱን እያጎላን፣ ለእነርሱ ቀዳዳ መክፈት አይገባንም። እርሱን ነው መከላከል ያለብን በአገራችን። የውስጥ ጥንካሬ ነው ዋናው ነገር፤ እነርሱ እጃቸውን የሚያስገቡበትን ቀዳዳ መዝጊያው መንገድ።
የተፋሰሱ አገራት በቅርብ አመታት ውስጥ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብለው ያምናሉ?
አሁን እኛ ትንሽ ጠንክረን መስራት ያለብን ነገር የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በተለይ ብሩንዲንና ኬንያን የተስማሙበትን ነገር በአገራቸው ፓርላማ ቢያፀድቁትና የአራቸው ህግ አካል ቢያደርጉት፣ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ቢቋቋም፣ የውሃ ድልድሉ ይጀመራል። እርሱ እንግዲህ አስገዳጅ ዓለም አቀፍ ህግ ውስጥ የሚካተት ነው የሚሆነው።ያ መፍትሄ ይሆናል።
አሁን ግብጾች እየተከላከሉ ያሉት ወደዚያም እንዳንደርስ ነው። ምክንያቱም እኛ ውሃ የማያስቀር ኃይል ማመንጫ እየሰራን እንኳ እንዲህ ከጮሁ የውሃ ድርሻ የሚያስቀር ነገር ከተፈጠረ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ከአሁኑ መገመት ይቻላል። መፍትሄው ግን የላይኛው የተፋሰስ አገራት የጀመሩትን ነገር አጠናክረው እነዚህ ብሩንዲና ኬንያ በፓርላማ አፀድቀው የአገራቸው ህግ ቢያደርገት፣ የግብጾች ጫና ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም ከሌሎቹ የላይኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር ይሆናል ቅራኔያቸው።
ስለዚህ ያኔ በአፍሪካ ሕብረትም የተሻለ ተሰሚነት ይሰጠናል። የሚያሳዝነው አሁን አፍሪካ ሕብረት ድረስ መጥተውም የቅኝ ግዛት ውሎችን እንዲፀድቅላቸውና በዚያ እንዲጠቀሙ መሞከራቸው ነው። ይኼ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ያላቸውን ንቀት ማሳያ ተደርጎ ነው የሚታየው እና አፍሪካውያንን በዚህ ጉዳይ ማነሳሳት በጣም ቀላል ጉዳይ ነው።
ስለዚህ በተፋሰሱ አገራት በኩል በፓርላማ አፀድቀን አስገዳጅ ሕግ አድርገን ከጨረስነው ይኼ ሁሉ አካኪ ዘራፍ ይቆማል።
ግብጽ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ሄዳ ጥያቄዋን አቅርባ ነበር ፤ ምክር ቤቱ ግን ወደ አፍሪካ ሕብረት መምራቱን መርጧል። የዚህንስ ጥቅም እንዴት ልንተረጉመው እንችላለን?
የፀጥታው ምክር ቤት እኮ ይኼ ለአካባቢው ስጋት አይደለም ብሎ ስለሚያምን ነው ወደ አፍሪካ የመለሰው። ሁለተኛ ወደ አፍሪካ ሕብረት ቢመለስም አሜሪካና የዓለም ባንክ አሁንም በታዛቢነት እየተሳተፉ ናቸው። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ወደ አፍሪካ ተመልሷል ማለት አይቻልም። ግን እስከዛሬ በአረብ አገሮች፣ በአውሮጳ አገራት፣ በአሜሪካ ሲንጠላጠሉ የነበሩትን በተወሰነ ደረጃ አስጥለናቸዋል። እና ለእኛ ይህ ትልቅ ነገር ነው። አሁንም ግን አፍሪካውያንን ማስተባበር፣ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን በማስተባበር ወደ ተሻለ ደረጃ መውሰድ የምንችልበት እድል ይከፍታል። ከዚህ በኋላ የፀጥታው ምክር ቤትም ይህንን ጉዳይ ለማየት ፈቃደኛ አይሆንም። እዚያው ጨርሱ ነው የሚሏቸው። እዚህ ደግሞ እኛ የተሻለ አቋም ላይ ነው ያለነው። የቅኝ ግዛት ውሎች የአፍሪካ ሕብረት እንዲያፀድቅላቸው አይጠበቅም።
የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ፣ የታችኛውና የላይኛው ተፋሰስ አገራትን በማስተባበር ረገድ ምን ማድረግ ነው ያለበት ይላሉ ታድያ?
አሁን በተለይ አሜሪካ የነበረችበትን ድርድሩ ከተቋረጠና ኢትዮጵያ ያንን ስምምነት አልፈርምም ካለች በኋላ ያለው አቋም ጥሩ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትን የምመክረው ባለሙያዎቹ ተደራዳሪዎቹ የሚሉትን በሙሉ ቢሰማና በዚያ መንገድ ቢንቀሳቀስ ነው። . . . እስከዛሬም ድረስ ጠንክረው እዚህ ያደረሱት ጥሩ ጥሩ ባለሙያዎች አሉን። [መንግሥት]እነርሱን ምክር መስማት አለበት። ወሳኙ ነገር እዚያ ላይ ነው ያለው።