ዐቃቤ ሕግ አምነስቲን በተቸበት ሪፖርት ላይ ከፊል ተዓማኒነት ያላቸው ጉዳዮች አሉ አለ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል 'ሕግ ከማስከበር በዘለለ' በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በከፊል ተዓማኒነት ያላቸው ክስተቶች እንዳሉበትና ሪፖርቱ ከመውጣቱ በፊት መንግሥት ለማረጋገጥ ምርመራ ሲከናወንባቸው የነበሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይህንን ያለው በግንቦት ወር ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ውስጥ ይፈጸማሉ ያላቸው የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ያወጣውን ሪፖርት በተመለከተ ቅኝት አድርጎ ያገኘውን ውጤት ይፋ ባደረገበት መግለጫው ላይ ነው።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሪነት መከናወኑ በተገለጸው የማጣራት ሥራ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት "መንግሥት ሕግ ለማስከበር የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድርጎ የማጠልሸት ዝንባሌ የሚስተዋልበት፣ በአብዛኛው ገለልተኘነት የጎደለው፣ የማስረጃ ምዘና ችግር ያለበት፣ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና ዐውድ ያላገናዘበ እንዲሁም መሠረታዊ ግድፈቶች ያሉበት" ነው ሲል ከሷል።

ነገር ግን መግለጫው የድርጅቱን ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አላደረገውም በዚህም መሰረት በዘገባው ውስጥ ከተካተቱት የመብት ጥሰት ወቀሳዎች የተወሰኑት በከፊልም ቢሆን ተዓማኒነት ያላቸው ሆነው መገኘታቸውን ገልጾ፤ "ከእነዚህ በከፊል ተዐማኒነት ካላቸው ጉዳዮች መካከል በርካቶቹ በመንግስት ታውቀው ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የምርመራ ሥራ ሲከናወንባቸው የነበሩ ናቸው" ብሏል።

መግለጫው በተጨማሪም ሪፖርቱ ገለልተኛነት የጎደለው፣ ተዓማኒነት የጎደላቸው የሆኑ ምስክርነቶችን በመያዝ እጅግ ውስብስብ በሆኑ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ዙሪያ የተሳሳቱ መደምደሚያዎች ላይ መድረሱን አመልክቶ፤ በሕግ ማስከበር ሂደት በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎችን የመብት ጥሰት አድርጎ ማቅቡንና "የሌሉ ጉዳዮች እንዳሉ በማስመሰል የሚያቀርብ መሆኑ . . . በአዘጋጆቹ ዘንድ ያለውን የፖለቲካ ወገንተኛነት ያሳያል" ብሏል።

በዐቃቤ ሕግ የቀረበው የዳሰሳ ሪፖርት የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት በአምነስቲ የወጣው ሪፖርት ግድፈቶች ያላቸውን የተለያዩ ጉዳዮች በማንሳት ተችቷል እንዲሁም ድርጅቱ የሪፖርቱን አዘገጃጀት እንዲመረምርም ጥያቄ አቅርቧል።

ከዚህ ባሻገርም ሪፖርቱ "ጉልህ ስህተቶች የተስተዋሉ ቢሆንም መንግሥት በሪፖርቱ ከተጠቀሱት የመብት ጥሰት ወቀሳዎች መካከል ተዓማኒነት ባላቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ቀደም ብሎ የጀመረውን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

በተያያዘም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች ይበልጥ እንዲከበሩ ከአገራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ትብብር ይቀጥላል ብሏል።

ቢቢሲ በዐቃቤ ሕግ የወጣውን ሪፖርት በተመለከተ ናይሮቢ የሚገኘውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጽህፈት ቤት ምላሽ እንዳለው ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፤ ድርጅቱ የወጣውን መግለጫ ተመልክቶ ምላሽ ለመስጠት ዕለቱ የሥራ ቀን ባለመሆኑ እንዳልቻሉና በቀጣይ ቀናት ምላሽ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።