ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ገንዘብ በማጭበርበር ተጠርጥሮ በኤፍቢአይ ከዱባይ ‘የተጠለፈው’ ናይጄሪያዊ ማነው?
ሬመን ኦሎሩናዋ ይባላል። ናይጄሪያዊ ነው። 2.5 ሚሊዮን የኢንስታግራም ተከታዮቹ ሬይ ሀሽፓፒ በሚለው ስሙ ያውቁታል። 37 ዓመቱ ነው።
በርካታ ሚሊዮን ዶላር በማጭበርበር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊነት በማስገባት በመጠርጠሩ ኤፍቢአይ ከዱባይ አግቶ እንደወሰደው ጠበቃው ተናግረዋል።
የአሜሪካው የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ሬመንን እንዲሁም በበይነ መረብ የገንዘብ ምዝበራ የተጠረጠረውን ኢላልኬን ጃኮብ ፖንሌ ይዟል። ኢላልኬን፤ ሚስተር ውድቤሪ በሚባል ቅጽል ስም ይታወቃል።
ግለሰቦቹ ከዱባይ የተያዙት ሰኔ ላይ ነበር። ሐምሌ 3 በቺካጎ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ እና አሜሪካ የወንጀል ተጠርጣሪን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት የላቸውም። የዱባይ ፖሊሶች እንደሚሉት ግን ከዚህ ቀደምም ተጠርጣሪዎች ለአሜሪካ ተላልፈው ተሰጥተዋል።
የአሜሪካ የፍትህ ተቋም ለቢቢሲ እንደተናገረው ሀሽፓፒ ከዱባይ ተባሯል እንጂ ለአሜሪካ ተላልፎ አልተሰጠም።
ጠበቃው ጋል ፒስተኪ በበኩላቸው ደንበኛቸው ኢንስታግራም ላይ ቅንጡ ሕይወቱን ከማሳየት ውጪ ወንጀለኛ አይደለም። ሀብቱን ያካበተውም በሕጋዊ መንገድ ነው ይላሉ።
“ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። ብዙ ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። ይወዱታል፤ ያከብሩታል። በዚህ ዘመን ይሄ [የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት] ንግድ ነው” ብለዋል ጠበቃው።
ኤፍቢአይ ክሱን የመሠረተው ‘ቢዝነስ ኢሜል ኮምፕሮማይዝ’ በመባል በሚታወቀውና በሌሎችም በይነ መረብን ባማከሉ ማጭበርበሮች ነው። በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት ሞክሯልም ይላሉ።
አሜሪካ የያዘችው በሕገ ወጥ መንገድ ነው?
ጠበቃው እንደሚሉት አሜሪካ ግለሰቡን ከዱባይ የመውሰድ ሥልጣን አልነበራትም ይላሉ።
“ኤፍቢአይ ከዱባይ ያገተው በሕገ ወጥ መንገድ ነው፤ በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ልውውጥ አልተደረገም። የፍርድ ቤት ሰነድም አልገባም። አሜሪካዊ አይደለም። አሜሪካ እሱን የመውሰድ ሥልጣን የላትም” ብለዋል።
የዱባይ ፖሊስ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች አሳልፎ በመስጠቱ ከኤፍቢአይ ዳይሬክተር ምስጋና እንደደረሰው በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
የአሜሪካ የፍትህ ተቋም ቃል አቀባይ ግን፤ የዱባይ ፖሊስ ለምን ጉዳዩን “የወንጀል ተጠርጣሪን አሳልፎ መስጠት” እንዳለው መናገር ያለበት ራሱ የዱባይ ፖሊስ ነው ብለዋል ለቢቢሲ።
ጠበቃው ግን ነገሩ አልተዋጠላቸውም። “ዱባይ ልታባርረው ከፈለገች መሄድ የነበረበት ወደ ናይጄሪያ ነበር” ብለዋል።
ሀሽፓፒ የተከሰሰው በምንድን ነው?
ሬይ ሀሽፓፒ ቅንጡ አኗኗሩን በኢንስታግራም በማሳየት ዝናን አትርፏል። ከታሰረ በኋላ 100,000 ተጨማሪ ተከታዮች አፍርቷል።
የዱባይ ፖሊስ እንደሚለው፤ ናይጄሪያዊው ሲታሰር 40 ሚሊዮን ዶላር፣ 13 እጅግ ዘመናዊ መኪኖች (6.8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ)፣ 21 ኮምፒውተር፣ 47 ተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲሁም ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ምዝበራ ሊካሄድባቸው እቅድ የተያዘ ሰዎች አድራሻ ተይዟል።
ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ነበር ከተባሉት መካከል የአሜሪካ የጠበቆች ተቋም፣ ባንክ እና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለብ ይገኙበታል።
ድንበር ዘለል የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች መሪም መሆኑንም በክሱ ተመልክቷል።
እነዚህ መዝባሪዎች የሰዎችን የግል መረጃ በመስረቅ፣ ሐሰተኛ የንግድ ድርድር በመፍጠር ወይም ሰዎች ወደተሳሳተ የባንክ ቁጥር ገንዘብ እንዲልኩ በማድረግ ይታወቃሉ።
በናይጄሪያ የወጣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግን ተከትሎ፤ ወንጀለኞቹ ‘419 ስካመርስ’ በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ።
419 ምንድን ነው?
በተለያየ መንገድ የሚከናወን ማጭበርበር ነው።
ለምሳሌ አንድ ሰው ገንዘብ ለማስተላለፍ እርዳታ እንዲያደርጉለት የሚጠይቅ ኢሜል ሊልክልዎ ይችላል። ባለበት አገር ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ወይም ተፈጥሯዊ አደጋ ገንዘብ መላላክን አዳጋች እንዳደረገበትም ይነግርዎታል። የባንክ ቁጥርዎን ከላኩለት ገንዘቡን እንደሚያስተላልፍልዎም ይገልጻል። ከዚያም ቁጥሩን ተጠቅሞ ገንዘብዎን ይዘርፋል።
የሀሽፓፒ ክስ እንደሚያሳየው፤ ሕገ ወጥ 14.7 ሚሊዮን ዶላር ወደ ሕጋዊነት ለማስገባት ከኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች ጋር ተመሳጥሯል።
ማልታ የሚገኝ ባንክ የተጠቀሰው ያህል ገንዘብ እንደጠፋበት ሪፖርት አድርጓል።
ኤፍቢአይ እንደሚለው ባለፈው ዓመት ብቻ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ከግለሰቦችና ከተቋሞች ተሰርቋል።
ዐቃቤ ሕግ ኒክ ሀና እንዳሉት፤ ክሱ በመላው ዓለም የዘራፊዎችን መንገድ የሚያዘዋውር ግለሰብን ይመለከታል።
የሀሽፓፒ ጠበቃ እንደሚሉት ከሆነ ግን ደንበኛቸው ገንዘቡን ያሰባሰበው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለውን ዝና ተጠቅሞ ነው፤ የፍርድ ሂደቱ ወራት ወይም ዓመትም ሊወስድ እንደሚችል አክለዋልል።
ሌላኛው ተጠርጣሪ ‘ሚስተር ውድቤሪ’
ሌላኛው በቁጥጥር ስር የዋለው ናይጄሪያዊ ኢላልኬን ጃኮብ ፖንሌ (ሚስተር ውድቤሪ) ነው። ጠበቃው ማይክል ቢ ናሽ ከደንበኛቸው ጋር ለመነጋገር ጊዜ እንዳልተሰጣቸው ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።
የ29 ዓመቱ ተጠርጣሪ ኢንስታግራም ላይ ‘ሚስተር ውድቤሪ’ የሚል ገጽ አለው።
ኤፍቢአይ እንደሚለው፤ ኢሜል የሚልከው ማርክ ኬይን በሚል ስም ሲሆን፤ በበይነ መረብ ገንዘብ በማጭበርበር ክስ ተመስርቶበታል።
አንድ ቺካጎ የሚገኝ ድርጅትን 15.2 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበሩ በክሱ ተመልክቷል። ከገንዘቡ ጥቂቱን በቢትኮይን በማስቀመጥ እንዳይደረስበትም ጥረት አድርጓል ተብሏል።