ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የለንደን ፖሊስ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ሐውልትን ያፈረሱትን እየተከታተለ መሆኑን አስታወቀ
በደቡብ ምዕራብ ለንደን ዊምብሌደን በሚገኝ ፓርክ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት በተወሰኑ ሰዎች መፍረሱ ይታወቃል፡፡
ፖሊስም ማክሰኞ ዕለት ምሽት በካኒዛሮ ፓርክ የተፈጠረውን ይህንን ወንጀል እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሐውልቱ ያፈረሱት 100 የሚጠጉ ሰዎች አንድ ላይ በመሰባሰብ እንደሆነ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የዊምብልደን ነዋሪ የሆኑት አንድሪው ሞሪስ፤ ከውሻቸው ጋር የእግር ጉዞ እያደረጉ ሳለ በፓርኩ ውስጥ የተሰባሰቡ ሰዎች መመልከታቸውንና ግለሰቦቹ መፈክሮችን እና በራሪ ወረቀቶችን ይዘው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አንድሪው አክለውም ሐውልቱ ሲፈርስ ድምጽ መስማታቸውን ጠቅሰው ምን እንደተፈጠረ ግን በዐይናቸው አለማየታቸውን አስረድተዋል፡፡
የከተማዋ ፖሊስ መረጃ የማሰባሰብና የምርመራ ሂደቱ እንደቀጠለ መሆኑንና እስካሁን ግን በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው እንደሌለ ገልጿል፡፡
ድርጊቱ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ ከተፈጠረ ተቃውሞ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የድምጻዊውን መገደል ተከትሎም በሐረር የሚገኘው የአጼ ኃይለ ሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ሐውልትም ለታቃውሞ በወጡ ቡድኖች ፈርሷል፡፡
አጼ ኃይለ ሥላሴ በጎርጎሮሳዊያኑ 1936 የጣሊያንን ወረራ ተከትሎ ለስደት እንግሊዝ ባመሩበት ወቅት የቆዩት እንግሊዝ ውስጥ ነበር፡፡ በዚያም ከእውቋ እንግሊዛዊት ቀራጺና ደራሲ ቤተሰቦች ጋር ይኖሩ በነበረበት ወቅት ሐውልታቸው በቀራጺዋ የተሰራ ሲሆን በኋላ ላይም በካኒዛሮ ፓርክ እንዲቆም ተደርጓል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በድምጻዊው ሞት የተቆጡና ብረትና ተቀጣጣይ ነገር ያዙ ወጣቶች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራና የሚዲያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ያለው ከበደ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ወጣቶቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማን በማውረድ ለማቃጠል መሞከራቸውን በምትኩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰንደቅ አላማ መስቀላቸውንና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
በኤምባሲው የቆንስላ ክፍል ውክልና ለመስጠት መጥቶ የነበረ አንድ ተገልጋይን ሲወጣ በማግኘት መደብደባቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
የወጣቶቹ ዋና አላማ ኤምባሲው በመግባት ጉዳት ማድረስ እንደነበር ያመላከቱት አቶ ያለው ተቀጣጣይ ነገርና ብረት ይዘው እንደነበር ለቢቢሲ አስረድተዋል፡፡