ትራምፕ ገነዘብ ነክ መረጃዎችን ለአቃቤ ህግጋት እንዲያስረክቡ ፍርድ ቤት ወሰነ

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገንዘብ ነክ መረጃዎችን ለኒውዮርክ አቃቤ ህግጋት እንዲያስረክቡ ውሳኔ አስተላልፏል።

አቃቤ ህግጋቱ ፕሬዚዳንቱ የሚሰጧቸው መረጃዎችንም በመመርኮዝ ከግብር ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ይመረምራሉ።

በተያያዘ ዜናም ይህ መረጃቸው ለኮንግረስ መሰጠት የለበትም የሚል ውሳኔም አስተላልፏል።

ከአራት አስርት አመታት በፊት መሪ የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን በኋላ ገንዘብ ነክ ወይም ከግብር ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ይፋ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ ትራምፕ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ናቸው።

የትራምፕ ጠበቆች በበኩላቸው ፕሬዚዳንቱ በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ መረጃዎችን ያለማሳየት መብት አላቸውም በማለት እየተከራከሩ ነው። ኮንግረስም የመጠየቅ ህጋዊ መሰረት የለውም እያሉ ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ፕሬዚዳንቱ ያለመጠየቅ እንዲሁም መረጃዎችን ያለማሳየት መብት አላቸው የሚለውን ውድቅ አድርጎታል፤ ከወንጀል ምርመራዎች ነፃ ሊሆኑ አይገባምም ብሏል።

"ከሁለት መቶ አመት በፊት የተመሰረተው የፍትህ ስርአታችን መሪም ይሁን ማንኛውም ዜጋ በወንጀል ምርመራዎች ሲጠየቅ መረጃዎችን ማስረከብ አለበት" በማለት ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

" ይህንን መርህ ዛሬ የምናረጋግጥበት ነው" ብሏል።

ትራምፕ በበኩላቸው ከግብር ጋር የተያያዘ ወንጀል ፈፅመዋል የሚለውን መሰረተ ቢስ ነው በማለት አጣጥለዋል፤ ምንም አልፈፀምኩም ሲሉ ክደዋል።

ሁለት የዲሞክራት ፓርቲ አባላት የሆኑ ተወካዮችና የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለአመታት ያህል ትራምፕ ከግብር ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ይፋ እንዲያደርጉ ሲጠይቁ ነበር።

ይህም መረጃም በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎችን በተመለከተ ያለው ህግ ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነም ለመፈተሽ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከሶስት አመታት በፊት ወሲባዊ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሁለት ሴቶችን ዝም ለማስባል ገንዘብ መከፈሉንና ይህንንም ክፍያ ለመሸፈን መረጃዎች ተፈብርከዋልም የተባለውንም ለማጣራትም ይረዳል ተብሏል።