የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ፖሊስ አስታወቀ

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው አለመረጋጋት የሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የፌደራልና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች አስታወቁ።

ባለመረጋጋቱ ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ የሚወጣው መረጃ ጭማሪ ቢያሳይም በፌደራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ በኩል እየወጣ ያለው አሃዝ ልዩነትን አንጸባርቋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር ለአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰጡት ያለውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው የሟቾች ቁጥር 239 ደርሷል።

ነገር ግን ቢቢሲ ይህንን አሃዝ ለማጣራት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት የሆኑትን አቶ ጄይላን አብዲን ጠይቆ ባገኘው መረጃ መሰረት የጸጥታ ኃይል አባላትን ጨምሮ የሟቾች ቁትር 177 መሆኑን ለመረዳት ችሏል።

በዚህም መሰረት 167 ሰዎቹ የሞቱት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲሆን የቀሩት 10ሩ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ 229 መሆናቸውን አቶ ጄይላን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከአለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ ከተፈጸሙ ጥቃቶችና የንብረት ውድመት የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ገልጾ፤ በኦሮሚያ ክልል 3100 ሰዎች እንዲሁም 1600 ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተይዘዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ተጠባባቂ ኮሚሽነሩ እንዳሉት እንዳሉት ግን ቁጥሩ "በክልሉ በተከሰተው አለመረጋጋት 14 የፖሊስና የሚሊሽያ አባላትና 215 ሰላማዊ ሰዎች ሞተዋል" በማለት ተናግረዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 166 መድረሱን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን የገለጹ ሲሆን በወቅት 167 የሚሆኑ ግለሰቦችም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረው ነበር።

ከሰኞ ሰኔ 22 ሌሊት ጀምሮ በተቀሰቀሰው አለመረጋጋት በቀናት ውስጥ ይህ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሮ 239 መድረሱም ተገልጿል።

በባለስልጣኑ ለህይወት መጥፋት ምክንያት ያሉት ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት እንዲሁም በተለያያዩ ብሔሮች መካከል ከተፈጠረ ሁከት የተያያዘ ነው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ተጠባባቂ ኮሚሽነሩ በክልሉ "የመንግሥት እንዲሁም የግል ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እንዲሁም ዝርፊያ ተፈፅሟል" ብለዋል።

መንግሥት ለደረሱት ጥፋቶች ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን 3 ሺህ 500 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሉም ተናግረዋል "እነዚህ ግለሰቦች ፀረ- ሰላም ኃይሎች ናቸው። የድምፃዊውን ሞት ሽፋን በማድረግ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፈራረስ ጥረት አድርገዋል፤ ጥቃቶችንም ፈፅመዋል" ብለዋል።

ፖሊስ ጨምሮም በግድያ፣ በሁከቱና በንብረት ማጥፋቱ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች በተጨማሪ አለመረጋጋቶቹ ተከስተው ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ነዋሪውን በመጠበቅ ኃላፊነታቸዉን ያልተወጡ የፀጥታ አባላትን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው ብሏል።

በፖለቲካ ግጥሞቹ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የተገደለው ሰኔ 22/2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ መኪናው ውስጥ ነበረ።

በግድያው ተጠርጥረው ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ቀርበው የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ሰዎች መያዛቸውን ገልጿል።