ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቬንዝዌላ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር አገሯን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
የቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በአገራቸው የአውሮፓ ኅብረትን ወክለው የሚገኙትን አምባሳደር ከአገሬ ይውጡልኝ ብለዋቸዋል። ሻንጣቸውን መሸከፊያ 72 ሰዓታት ሰጥተዋቸዋል።
ማዱሮ ይህን እርምጃ በአምባሳደር ኢዛቤል ፔድሮሳ ላይ የወሰዱት የአውሮፓ ኅብረት በ11 የቪንዝዌላ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ ነው።
ባለሥልጣናቱ ላይ ማዕቀቡ የተጣለው በተቃዋሚው መሪ ጆዋን ጓይዶ የሚመራውን የብሔራዊ ሸንጎን አልታዘዝ ብላችኋል፣ ለማፍረስ ሞክራችኋል፣ ዲሞክራሲን ንዳችኋል በሚል ነው።
ወጣቱ ጓያዶ ራሱን የቬንዝዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አድርጎ ነው የሚመለከተው። በርካታ ምዕራብ አገራትም እውቅና ሰጥተውታል። አገሪቱን እያስተዳደሩ የሚገኘት ግን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ናቸው።
የላቲን አሜሪካ ጎረቤት አገራትን ጭምሮ 50 የዓለም አገራት ፕሬዝዳንት ማዱሮን እውቅና ነፍገው ለወጣቱ ጓይዶ ሙሉ እውቅና ሰጥተዋል።
ጓይዶ ማዱሮን ለመገልበጥ በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርግም አልተሳካለትም።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት እውቅና የሰጡት ጓይዶ የዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ድጋፍን እያገኘ ያለ ተቃዋሚ መሪ ነው።
ኒኮላስ ማዱሮ ሰኞ በቴሌቪዥን ቀርበው ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ ኅብረትን ኮንነዋል። "ለውድ አገራችን ቬንዝዌላ ክብር ከሌላቸው፣ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው፣ ከአገራችን ውልቅ ብለው መውጣት ይችላሉ" ብለው ነበር አምባሳደሯን።
ጨምረውም "አውሮፕላን ተውሰንም ቢሆን አገራችንን እንድትለቅ እናደርጋለን" ብለዋል ማዱሮ።
በአሁኑ ሰዓት የቬንዝዌላ የአየር ክልል በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዝግ ሆኖ ነው የሚገኘው።
አሁን ማዕቀብ የተጣለባቸው 11 ባለሥልጣናትን ጨምሮ 36 የቬንዝዌላ ሹመኞች በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
ቬንዝዌላ ምዕራባዊያን በጣሉባት ማዕቀብ የተነሳ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ የምትገኝ አገር ናት። አራት ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝቧ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ አገር ለቆ ተሰዶባታል።
ቬንዝዌላ የነዳጅ ሀብታም ብትሆንም የሥራ አጥ ቁጥሯ ከፍተኛ ነው። በአገሪቱ መድኃኒት እንደልብ ማግኘትም የማይታሰብ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ቬንዝዌላዊያንም የምግብ እርዳታን የሚሹ ናቸው።