ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካው ዩኒቨርስቲ ለመረጃ መዝባሪዎች 1.14 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተገደደ
ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ካሉ ቀደምት የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ዩኒቨርስቲ ያሉትን መረጃዎች ለማዳን ሲል ለኢንትርኔት የመረጃ መዝባሪዎች (ሐከርስ) በድብቅ ከተደረገ ድርድር በኋላ 1.14 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉን አመነ።
የካሊፎርኒያው ሳንፍራንሲስኮ ዩኒቨርስቲ የምዝበራ ጥቃቱ የተሰነዘረበት በፈረንጆቹ የሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ 'ኔትዎከር' በተባለው የወንጀለኛ ቡድን ነው።
የዩኒቨርስቲው የኮምፒውተር ባለሙያዎች ለመረጃ ምዝበራው የተለቀቀው ቫይረስ በዩኒቨርስቲው ኮምፒውተሮች ላይ ከመሰራጨቱ በፊት ለማስቆም ጥረት አድርገው ነበር።
ከዚህ ክስተት በኋላ ዩኒቨርስቲው ከመረጃ ሰርሳሪዎቹ ጋር በድብቁ የበይነ መረብ ክፍል እየተደራደረ መሆኑን ማንነቱ ያልታወቀ ሰው መረጃውን ለቢቢሲ በማቀበሉ ቢቢሲ ድርድሩን ለመከታተል ችሏል።
ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ይህ 'ኔትዎከር' የተባለው የመረጃ መዝባሪ ቡድን ቢያንስ በሌሎች ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ላይ ለገንዘብ ሲል የመረጃ መረብ ጥቃቶችን ፈጽሟል።
የመረጃ መዝባሪዎቹ ከተቋማት እጅግ ጠቃሚ መረጃዎችንና በገንዘብ የማይተመኑ የምርምር ስራዎችን በመስረቅ በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ከባለቤቶቹ ጋር በድብቁ የኢንተርኔት ዓለም ላይ በሚያስቀምጡት የጊዜ ገደብ የሚፈልጉትን ገንዘብ ይጠይቃሉ።
በዚህም የተቀመጠው ጊዜ ሲያበቃ የጠየቁት የገንዘብ መጠንን በዕጥፍ ያሳድጉታል ወይም የሰረቁትን መረጃ ያወድሙታል።
ዩኒቨርስቲው በድብቅ መረጃ ከመዝባሪዎቹ ጋር ባደረገው ድርድር ተቋሙ በዓመት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ እንዳለው የተረዱት ተደራዳሪዎች በመጀመሪያ ላይ መረጃውን ለመመለስ የ3 ሚሊዮን ዶላር ክፍያን ጠይቀው ነበር።
ዩኒቨርስቲውም በተደራዳሪው በኩል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዩኒቨርስቲው ገቢ ላይ ከባድ የሆነ የገንዘብ ተጽእኖን መፍጠሩን ለመዝባሪዎቹ በማስረዳት 780 ሺህ ዶላር እንዲቀበሉት ጠይቆ ነበር።
ለአንድ ቀን በተደረገው ድርድር ዩኒቨርስቲው ያለውን ገንዘብ በሙሉ አሰባስቦ 1.02 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ቢስማማም ወንጀለኞቹ ግን ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር በታች እንደማይቀበሉ አሳወቁ።
ከሰዓታት በኋላም ዩኒቨርስቲው ቀድሞ በሰጠው የገንዘብ መጠን ላይ ጭማሪ በማድረግ በመጨረሻ መክፈል የሚችለውን ገንዘብ መጠን 1,140,895 ዶላር በማሳደግ መረጃውን ለዘረፉበት ወንጀለኞች ለመክፈል ተስማማ።
በቀጣዩ ቀንም በበይነ መረብ በኩል 116.4 ቢትኮይን ከዩኒቨርስቲው ወደ መረጃ መዝባሪው ቡድን 'ኔትዎከር' መተላለፉን የሚገልጽ መረጃ ደርሷቸዋል።
የካሊፎርኒያው ሳንፍራንሲስኮ ዩኒቨርስቲ ክፍያውን ከፈጸመ በኋላ በመዝባሪዎቹ ጥቃት የተፈጸመበትን የኮምፒውተር ሥርዓቱንና መረጃዎቹን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራውን እያከናወነ ኤፍቢአይ በወንጀል ድርጊቱ ላይ ለሚያደርገው ምርመራ ድጋፍ እየሰጠ ነው።
ዩኒቨርስቲው ስለክስተቱ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "የተመዘበሩት መረጃዎች ዩኒቨርስቲው ሲያከናውናቸው የነበሩ ሕዝባዊ ጠቃሜታ ያላቸው የምርምር ሥራዎች ናቸው። በዚህም ምክንያት አስቸጋሪ ውሳኔ በመወሰን መረጃዎቻችንን ለማስለቀቅና ለማስመለስ 1.14 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተገደናል" ብሏል።
የመረጃ ደኅንነት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሕግ አስከባሪ አካላት ከሚሰጡት ምክር በተቃራኒው ተቋማት ከመረጃ መዝባሪዎች ጋር ድብቅ ድርድር እያደረጉ መሆኑን ይገልጻሉ።