ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉግል ሰዎች በኢንተርኔት የጎለጎሉትን ምስጢር መሰረዝ ሊጀምር ነው
ጉግል በቀደመ አሰራሩ ደንበኞቹ ያሰሷቸውን የበይነመረብ አድራሻዎችን ዝርዝር ቅጂ ያስቀር ነበር፡፡ ይህ ነገር ቅሬታን ሲፈጥር ቆይቷል፡፡
የደንበኞቹን ቅሬታ ተከትሎ ጉግል ኩባንያ አሰራሩን ለመቀየር ቃል ገብቷል፡፡
ደንበኞች የነካኩት መተግበሪያ፣ ያሰሱት ድረገጽና የጎበኟቸው የበይነመረብ አድራሻዎች በሙሉ የት ቦታና በምን ኮምፒውተር አሰሳ እንደተደረገባቸው ጭምር ሰዓቱንና አገሩን ሳይቀር ቋት ውስጥ ያስቀር ነበር፣ ጉግል፡፡
የማስታወቂያ ገቢ ምንጭ የሚሆውም ይኸው የደንበኞች መረጃ ስብስብ ነው፡፡
አሁን ግን ጉግል እነዚህን የደንበኛ መረጃዎች ቢበዛ ለ18 ወራት ካቆያቸው በኋላ ራስ በራሳቸው እንዲጠፉ አሰራሩን ቀይሯል፡፡
አንድ ደንበኛ ዩትዩብ ላይ ምን እንደተመለከተና ለስንት ሰዓት ያህል ቪዲዮውን በማየት እንደቆየ ጭምር ይመዘግብ የነበረው ጉግል አሁን ግን እንዲህ ዓይነት የዩትዩብ ደንበኛ ምስጢሮች ከ36 ወራት በኋላ ይሰረዛሉ ብሏል፡፡
ጉግል የዩትዩብ ቪዲዮዎች የሐሰሳ ታሪክ ከሌሎች የሐሰሳ ታሪኮች ዘለግ ላለ ጊዜ ሳይሰረዙ እንዲቆይ የፈለገው በሰዎች የዳሰሳ ልማድና ታሪክ በመመስረት ለደንበኞቹ የሚመቻቸውን የሙዚቃ ምርጫዎች ለማቅረብ እንዲያስችለው ነው፡፡
የአንድ ሰው የዩትዩብ ሐሰሳ ታሪክ ተመዝግቦ ሲቆይ ጉግል ለደንበኞቹ ተስማሚ ቪዲዮችን እንዲጋብዝ ያግዘዋል፡፡
እነዚህ አሰራሮች አዲስ የጉግል አድራሻ ለሚያወጡ ብቻ የሚተገበሩ አሰራሮች ሲሆኑ ከዚህ ቀደም የጉግል ወይም የዩትዩብ ወይም የጂሜይል አድራሻ የነበራቸውና የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ግን ‹‹ሴቲንግ›› እንዲቀይሩ የሚጠይቅ ማስታወሻ በቅርቡ ይላክላቸዋል ብሏል ፣ጉግል፡፡
ይህ እርምጃ በጉግል ኩባንያ እንዲወሰድ ያስቻለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰው ፊትን እንደ መለያ የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎች ላይ ቅሬታና ተቃውሞ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ ነው፡፡