ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካዋ የሉዊዚያና ግዛት ውርጃን የሚገድበው ሕግ ተሻረ
የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሉዊዚያና ግዛት ውርጃን የሚከለክለው ሕግ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው በማለት ሽሮታል።
በተሻረው ሕግ መሰረት ዶክተሮች ጽንስ ለማቋረጥ የሚፈልጉ ሴቶችን አቅራቢያቸው ወደ ሚገኙ ሆስፒታል እንዲገቡ የሚያደርግ ሲሆን ይህ አሰራር ሴቶቹን ላልተፈለገ ችግር አጋልጧቸዋል ብለዋል ብይኑን ያስተላለፉት ዳኞች።
ዋና ዳኛ ጆን ሮበርትስን ጨምሮ ሌሎች አራት ዳኞች ድምጻቸውን በመስጠት ሕጉ 5 ለ 4 በሆነ ድምጽ እንዲሻር ሆኗል።
በአውሮፓውያኑ 2016 በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ በቴክሳስ ውርጃን የሚፈቅድ ሕግ አስተላልፏል።
በትራምፕ አስተዳደር ዘመን እንዲህ አይነት ከፍተኛ የውርጃ ሕግ ሲሻር ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተጠቁሟል።
2014 ላይ የወጣው ሕግ በሉዊዚያና የሚገኙ ዶክተሮች እስከ 48 ኪሎ ሜትር ድርስ ባሉ አካባቢዎች ጭምር ባሉ ሆስፒታሎች ስልጣን ያላቸው ሲሆን ግዛቲቱ ይህን ያደረግኩት የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ ነው ብላ ነበር።
ነገር ግን ተቺዎች እንደሚሉት ይህ አከራካሪው ሕግ ውርጃን የሚፈጽሙ ሆስፒታሎችን ቁጥር የቀነሰና የሴቶችን መብት የሚጥስ ነው።
በቀደመው ሕግ መሰረት የጽንስ ማስወረድ መፈጸም የሚፈልጉ ሴቶች በአቅራቢያቸው እስከ 48 ኪሎሜትር ድረስ ባሉ ሆስፒታሎች ብቻ ውርጃውን መፈጸም አለባቸው።
ምንም እንኳን ግዛቲቱ ሕጉን ጠበቅ ያደረግኩት የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ ነው ብትልም ተሟጋቾች ግን በውርጃ ወቅት ሊያጋጥም የሚችለው የጤና እክል እምብዛም ነው ይላሉ።
በተጨማሪም በዚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሆስፒታሎች ከሐይማኖት ጋር ግንኙነት ያላቸው አልያም ወግ አጥባቂ በመሆናቸው በሆስፒታሉ ውስጥ ውርጃ እንዲፈጸም አይፈቅዱም ብለዋል።
ይህ ደግሞ ሴቶች የተሰጣቸውን ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል በማለት ይከራከራሉ።
የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በአዲሱ ሕግ ምክንያት ማንኛውም ክሊኒክና ሆስፒታል አይዘጋም አልያም ላለመዘጋት ሲሉ ውርጃ እንዲፈጽሙ አይገደዱም ብሏል።