ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ድርድራቸውን ለማጠናቀቅ ተስማሙ

የህዳሴው ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር ለማጠናቀቅ ሲስማሙ ኢትዮጵያም ከሁለት ሳምንት በኋላ የውሃ ሙሌት ለመጀመር እንዳቀደች አስታውቃለች።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ ሦስቱ አገራት ድርድራቸውን በማጠናቀቅ ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ መወሰናቸውን አመልክቷል።

ጨምሮም ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለመጀመር ዕቅድ የያዘች መሆኑን አመልክቶ በዚህ ጊዜም ቀሪ የግንባታ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ ገልጿል።

በዚህ የሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥም ሦስቱ አገራት መቋጫ ባለገኙ ቀሪ ጉዳዮች ላይ ድርድራቸውን በማካሄድ ከስምምነት እንዲደረስ ትናንት በነበረው ውይይት ላይ እንደተስማሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አመልክቷል።

በውይይቱ ላይ አገራቱ ጉዳያቸው በአፍሪካ ሕብረት እንደተያዘ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እንዲያሳቁና ሦስቱም አገራት አላስፈላጊ ከሆነ የመገናኛ ብዙሃን ውዝግብ እንዲቆጠቡ ተጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ [ዶ/ር] በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሉት በደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ መሪነት ትናንት ምሽት በሦስቱ አገራት መሪዎች መካከል በተደረገው ውይይት ላይ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት አገራቱ ድርድራቸውን እንዲያጠናቅቁ ተስማምተዋል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሮይተርስ፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በሚደረግ ድርድር ከስምምነት ላይ ሳይደረስ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት እንዳትጀምር ከስምምነት ላይ መደረሱን ዘግቧል።

ሮይተርስ ከግብጽ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የወጣን መግለጫ ጠቅሶ፤ በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ በተናጠል ግድቡን በውሃ መሙላት እንደማትጀምር ገልጿል።

ሮይተርስ ጨምሮም "ለሚደረገው ድርድር ስኬት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃ እንደማትወስድ" የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ እንደተናገሩ የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል ብሏል።

የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒም በጉዳዩ ላይ እንደዘገበው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ግዙፍ ግድብ በውሃ የመሙላት ዕቅዷን እንደምታዘገየው የግብጽ ፕሬዝዳንትን ጠቅሷ ገልጿል።

ኤኤፍፒ በተጨማሪም የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ "አገራቱ በድርድር ከስምምነት እስኪደርሱ ድረስ ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሥራ እንዲዘገይ ስምምነት ተደርሷ" ማለታቸውን ዘግቧል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዳለው ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሃሳብ መሰረት ከሦስቱም አገራት የተወጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ አጠቃላይ የስምምነት ሃሳብ ለማቅረብ ይሞክራሉ።

ቢቢሲ፤ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እየወጡ ስላሉት መረጃዎች ለማጣራት ጥረት እያደረገ ነው።

በኢትዮጵያ በኩል ግን የውሃ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት በአገራቱ መካከል ውይይት መደረጉንና በዚህም መሰረት በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥ ድርድራቸውን ለመቋጨት መስማማታቸውን እንጂ የግድቡን ውሃ ሙሌት መዘግየትን በተመለከተ ያሉት የለም።

ኢትዮጵያ ግንባታውን እያጠናቀቀችው ያለው ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሦስቱ አገራት መካከል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ያለውጤት እስከ ዛሬ ደርሷል።

ከሳምንት በፊት በኢንተርኔት አማካይነት ሲደረግ የነበረው ድርድር ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት በመውሰዷ መቋረጡ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት ሥራ በመጪው ሐምሌ ወር ዕቅድ መያዟን ከወራት በፊት ያስታወቀች ሲሆን ከግብጽና ከሱዳን ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት 'አገሪቱ ከየትኛውም ወገን የሚሰጥን ይሁንታ ሳትጠብቅ በያዘችው ዕቅድ መሰረት ግድቡን በውሃ መሙላት እንደምትጀምር' አስታውቆ ነበር።