ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተስፋ የተጣለበት የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰዎች ላይ እየተሞከረ ነው
በሙከራ ላይ የሚገኘውና ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የኮሮናቫይረስ ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም በጎ ፈቃደኞች ላይ እየተሞከረ ነው።
በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ለ300 ሰዎች ላይ ይሰጣል የተባለውን ክትባት የሚመሩት ከኢምፔሪያል ኮሌጅ ሎንዶን ፕሮፌሰር ሮቢን ሻቶክ ናቸው።
ክትባቱ በሰዎች ላይ ከመሞከሩ በፊት በእንሰሳት ላይ ተሞክሮ አበረታች ውጤት አሳይቷል። ክትባቱ ጉዳት እንደማያስከትልና ሰውነት የመከላከያ ሴሎችን እንዲያመርት እንደሚያነቃቃው በእንሰሳት ላይ በተደረገው ሙከራ ተረጋግጧል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ከዚህ ሙከራ በፊት በሰው ላይ ክትባታቸውን እየሞከሩ ይገኛሉ።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ክትባት ሙከራ እየተደረገ ያለው በመላው ዓለም ነው። በዓለም ዙሪያ በትንሹ 120 የክትባት ሙከራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ከአፍሪካ ይህ ሙከራ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ በጎ ፈቃደኞች እየተወሰደ ነው።
የኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ክትባት ዛሬ በዩናይትድ ኪንግደም ሲጀመር የ39 ዓመቷ የፋይናንስ ባለሞያ ካቲ ከመጀመሪያዎቹ በጎ ፈቃደኞች አንዷ ሆና ተመዝግባለች።
ለምን በጎ ፈቃደኛ መሆን እንደፈለገች ከቢቢሲ ተጠይቃ "ተህዋሱን ለመዋጋት የእኔን ሚና መጫወት ስለፈለኩ ነው" ብላለች።
በዚህ ረገድ የእኔ ሚና ምን መሆን እንዳለበት አላውቅም ነበር፤ ይህ አጋጣሚ ሲፈጠር ፈቃደኛ ለመሆን አላቅማማሁም ብላለች።
በዚህ የመጀመሪያ ዙር ሙከራ የሚታዩ ውጤቶች ከተመዘገቡ በኋላ በሚቀጥለው ጥቅምት ክትባቱ ሌሎች 6ሺህ ሰዎችን እንዲያሳትፍ ተደርጎ ይሞከራል።
የኢምፔሪያል ኮሌጅ ሳይንቲስቶች ተስፋ እንደሚያደርጉት ክትባቱ ስኬታማ ከሆነ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ በመላው ዓለም መሰራጨት ይጀምራል።
በአሁን ሰዓት በመላው ዓለም 120 ቤተሙከራዎች ክትባት ለማግኘት እየሰሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከቤተ ሙከራ አልወጡም።
በክሊኒካል ሙከራ ደረጃ የሚገኙት 13 ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 5ቱ በቻይና፣ 3 በአሜሪካ፣ 2 በዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በጀርመን፣ በአውስትራሊያና በሩሲያ አንድ አንድ ይገኛሉ።
አሁን በዩናይትድ ኪንግደም እየተደረጉ ላሉት ሁለት ሙከራዎች 46 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት እንደተመደበላቸው ተነግሯል።