በቻይና 12 ሺህ ሲኒማ ቤቶች የመዘጋት ስጋት ተጋርጦባቸዋል

ኮሮናቫይረስ የሰዎችን እንቅስቃሴ በአያሌው መግታቱ ይታወቃል። በተለይም ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው እንደ ሲኒማ ቤት ያሉት በዚህ ረገድ ዋነኛ ተጎጂዎች ሆነዋል።

የቻይና ፊልም ማኅበር ከዚህ ወዲህ ሰዎች ወደ ሲኒማ የመመለስ እንድላቸው አነስተኛ ነው ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ የሲኒማ ውጤቶችን በኢንተርኔት ማቅረብ እየተለመደ በመምጣቱ ነው። ሌላው ምክንያት ቫይረሱ ሰዎችን ፍርሃት ውስጥ በመክተቱ ነው።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኙ ጊዜ ቻይና ሲኒማ ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ አዝዛ ነበር።

በዚህ ወቅት ሚሊዮን ቻይናዊያን ፊልምን በኢንተርኔት የመመልከት ልማድን አዳብረው ቀይተዋል። ይህ ለሲኒማ ቤቶች መልካም ዜና አልሆነም።

በአሁን ሰዓት በመላው ቻይና በትንሹ 12 ሺህ ሲኒማ ቤቶች ይገኛሉ። ባለፉት አስር ዓመታት ይህ ቁጥር በእጥፍ እንዳደገ ይገመታል። ምክንያቱ ደግሞ ቻይና ሲኒማን በፖሊሲ ደረጃ እያበረታታች በመምጣቷ ነው።

ሆኖም በቅርቡ የቻይና ፊልም ማኅበር ባደረገው አንድ የዳሰሳ ጥናት ከ10 ሲኒማ ቤቶች አራቱ የመዘጋት እጣ ተጋርጦባቸዋል። ይህ ማለት በትንሹ 5 ሺህ ሲኒማ ቤቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከገበያ ሊወጡ ይችላሉ።

በቻይና ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የእንቅስቃሴ ገደቦች ቀስ በቀስ እየተነሱ ሲመጡ በመጨረሻው ምዕራፍ ወደ ሥራ ይመለሳል ተብሎ የሚጠበቀው ሲኒማ ነው።

የቻይና መንግሥት ሲኒማም ሆነ ሌሎች በዝግ አዳራሽ የሚካሄዱ የመዝናኛ ከኩነቶች በውስን ተመልካቾች ብቻ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ፈቅዷል።

ሲኒማ ቤቶቹ እስከመጪው ጥቅምት ድረስ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ካልተመለሱ የሚያገኙት ዓመታዊ ገቢ በ91 በመቶ ሊቀንስ ይችላል።

ቻይና ባለፈው ዓመት ብቻ በሲኒማ ትኬት ሽያጭ ከ7 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ገቢ አስገብታለች።

በቻይና ለሲኒማ ቤቶች በቀጣይ ዓመታት ትልቁ ፈተና ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የኢንተርኔት ሲኒማ ነው። ምክንያቱም በኢንተርኔት በርካታ ፊልም ለማየት በ2 ዶላር ፓኬጅ መግዛት ሲቻል የአንድ ሲኒማ ቤት ትኬት ዋጋ ግን እስከ 20 ዶላር ድረስ ውድ ነው።

በዚህ ላይ የወረርሽኙ ስጋትን ታክሎበት ቻይናዊያን ወደ ሲኒማ ቤት ለመሄድ እጅግ ዳተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ሻውን ሬይን የቻይና የገበያ ጥናት ተቋም ባለቤት ነው። እሱ እንደሚለው በኢንተርኔት የሚታዩ ፊልሞች እነ አሊባባን በመሰሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ስለሚደጎሙ ርካሽ ናቸው። ሲኒማ ቤት ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ ከቢዝስነስ ሊወጣ የሚችልበት ዕድልም ሰፊ ነው።

ሌላው ፈተና አዳዲስ ፊልሞች በወረርሽኙ ምክንያት መሰራት ሳይችሉ ስለቀሩ ሰዎችን አባብሎ ወደ ሲኒማ ቤት የሚያመጣቸው ነገር ለጊዜው የለም።

የአዳዲስ ፊልሞች አለመኖር ወትሮም የተዳከመውን የሲኒማ ገቢ የበለጠ እንደሚጎዳው እንደሚያዳክመው እሙን ነው። አዳዲስ ፊልሞችን ለመስራት ደግሞ የበጀት እጥረት ማነቆ ሆኗል።

የቀድሞው የተንቀሳቃሽ ሲኒማ ኮርፖሬሽን ፕሬዝዳንት ክሪስ ፌንተን በበኩሉ ሲኒማ ቤቶች አብቅቶላቸዋል የሚባለው አስተሳሰብ ጨለምተኛ ነው ይላል።

ቻይናዊያን ፊልም በኢንተርኔት ሊያገኙት ይችሉ ይሆናል። ሲኒማ ቤት መሄድ ግን አንድ የተለመደ ባሕል ነው። ያ በምንም ሊተካ አይችልም። ነገ ለሲኒማ ብሩህ ጊዜ ነው የሚታየኝ ይላል።