ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የወባ በሽታ በአማራ ክልል 25 ወረዳዎች በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ተነገረ
በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሃያ አምስት ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ገለጸ።
የወባ በሽታው ካለፉት ሁለት ዓመታት ከፍ ባለሁኔታ በወረርሽኝ ደረጃ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች መከሰቱን ለቢቢሲ የገለጹት የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም የወባ ክፍል ባለሙያ አቶ አማረ ደስታ ናቸው።
"በዚህ ዓመት ወባ በክልሉ ከአምናውም ሆነ ከካቻምናው በበለጠ ጨምሯል" ያሉት ባለሙያው በተለይ በቋራ መተማ፣ ምሥራቅ ደምቢያ፣ ጎንደር ዙሪያ፣ ጃዊ፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ ደብረ ኤልያስ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ራያ ቆቦ፣ ቃሉ እና አበርገሌን የመሳሰሉ ወረዳዎች በሽታው በጣም ከጨመረባቸው አካባቢዎች ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል።
ለወባ በሽታው መስፋፋት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን በተለይ ቀደም ሲል በሽታውን ለመከላከል ይወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች መላላታቸውና በሽታውን ለመከላከል ኅብረተሰቡ ያደርጋቸው የነበሩ ጥንቃቄዎች መቆመቀቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ከእነዚህ መካከልም "ወባ ጠፍቷል በሚል የአጎበር አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ፣ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን አለማጽዳት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የጤና ኬላዎች ትኩረት መቀነስ" ለወባ በሽታ ክስተት መጨመር በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
በክልሉ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የወባ ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የጤና ጥበቃ ሚንስቴር 260 ሺህ ኪሎ ጸረ ወባ ኬሚካል መላኩን አቶ አማራ ደስታ አስታውቀዋል።
ከአማራ ክልል 80 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ መራቢያ ምቹ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን 68 በመቶው ነዋሪም ለበሽታው ተጋላጭ ነው ተብሏል።
በክልሉ ከመስከረም እስከ ታኅሳስ ድረስ ወራት የወባ በሽታ በስፋት የሚከሰት ሲሆን ከመጋቢት እስከ ሰኔ ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ እንደሚከሰት ታውቋል።