ኮሮናቫይረስ: የዓለምን ታሪክ የቀየሩ አምስት አደገኛ ወረርሽኞች

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለምን ታሪክ እየቀየረ ነው። ቢሊዮኖች አኗኗራቸው ከወራት በፊት ከሚያውቁት የተለየ ሆኖባቸዋል። ኮሮናቫይረስ ወደፊት በታሪክ ከሚጠቀሱ ክስተቶች አንዱ መሆኑ አያጠራጥርም።

ኮሮናቫይረስ የዓለምን ታሪክ የቀየረ የመጀመሪያው ወረርሽኝ አይደለም። እስቲ ዋና ዋና ከሚባሉት አምስቱን ከታሪክ መዛግብት እናገላብጥ።

ጥቁሩ ሞትና የአውሮፓ ሥልጣኔ

በግሪጎሪ አቆጣጠር በ1350 ላይ አውሮፓን የመታው ጥቁሩ ሞት ተብሎ የሚታወቀው [የቡቦኒክ ትኩሳት] ወረርሽኝ የአህጉሪቱን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ እንደቀጠፈ ይነገራል። አብዛኞቹ ሟቾች ደግሞ ለመሬት ባላባቶች እየሠሩ የሚያድሩ ገባሮች ነበሩ።

ከበሽታው በኋላ ግን የሠራተኞች ዋጋ እጅግ ተወደደ። ይህም በምዕራብ አውሮፓ የፊውዳል ሥርዓት እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል ይባላል። ይህ መላ ያሳጣቸው የመሬት ባላባቶች በሰው ፈንታ ቴክኖሎጂ ወደመጠቀም ገቡ።

ይህ ሂደት ምዕራብ አውሮፓ ወደ ሥልጣኔ እንደትገባ አድረጓታል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ምዕራብ አውሮፓውያን ዓለምን ለማሰስ ወደ ሌሎች አገራት ማቅናት የጀመሩትም በዚህ ወቅት በመሆኑ ወረርሽኙ ለቅኝ ግዛትም ሚና እንደተጫወተ ይገመታል።

ፈንጣጣና የአየር ንብረት ለውጥ

በ15ኛው ክፍለ ዘመን የደቡብ አሜሪካ አገራት በቅኝ ገዢዎች እጅ ስር መግባት ለዓለም የአየር ንብረት መለወጥ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አጥኚዎች የደቡብ አሜሪካ አገራት በአውሮፓውያን ቅኝ በመገዛታቸው ሳቢያ የሕዝብ ቁጥሩ ከ60 ሚሊዮን ወደ 6 ሚሊዮን ዝቅ ብሏል ይላሉ።

በርካቶች የሞቱት ቅኝ ገዥዎች ይዘዋቸው በመጡ በሽታዎች ሳቢያ ነው። በጣም ብዙ ሰው የቀጠፈው ፈንጣጣ እንደሆነ ታሪክ ይናገራል። በተጨማሪም ኩፍኝ፣ ኮሌራ፣ ወባና ታይፈስ ቅኝ ገዢዎች ለደቡብ አሜሪካ ሰዎች ያዛመቷቸው በሽታዎች ናቸው።

የቅኝ ገዢዎቹ ጣጣ ከደቡብ አሜሪካ አገራት አልፎ ለዓለም ሕዝብም ተርፏል። ነገሩ እንዲህ ነው፤ በሽታው ከቀጠፋቸው መካከል አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ነበሩ። በዚህ ምክንያት በርካታ የእርሻ መሬቶች ወደ ጫካነት ተቀየሩ።

በወቅቱ ከእርሻ መሬትነት ወደ ጫካነት የተቀየረው መሬት ስፋት ኬንያን ወይም ፈረንሳይን የሚያክል እንደሆነ ይገመታል። ይህ ክስተት የዓለምን ሙቀት መጠን ከተገቢው በላይ ቀነሰው። ምድርም ቅዝቃዜ እንደወረራት ይነገራል።

በዚህ ምክንያት በሌሎች ዓለማት ያሉ ሰዎች ተጎዱ። ሰብሎች ውርጭ መታቸው። በጣም የሚገርመው በዚህ የዓለም ሙቀት መቀነስ እጅግ የተጎዳችው ምዕራብ አውሮፓ መሆኗ ነው።

ቢጫ ወባና የሄይቲ አብዮት

በ1801 በአህጉረ አሜሪካ በምትገኘው አገር ሄይቲ የተከሰተው የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ትንሿ አገር የፈረንሳይን ቅኝ ገዢዎች ፈንቅላ እንድታስወጣ ምክንያት ሆኗል።

የፈረንሳዩ መሪ ናፖሊዎን ቦናፓርቴ እራሱን የዕድሜ ልክ መሪ አድርጎ ሾመ፤ አልፎም ደሴቷ ሄይቲን እንዲቆጣጠሩለት በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ላከ።

የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ግን ለወታደሮችም አልተመለሰም። በሽታው 50 ሺህ ገደማ የፈረንሳይ ወታደሮችን ቀጠፈ። ሐኪሞችና አሳሾችም በበሽታው ከሞቱት መካከል ነበሩ። ወደ ፈረንሳይ በሕይወት የተመለሱት 3 ሺህ ብቻ እንደሆነ ታሪክ ያሳያል።

አውሮፓውያን ምንጩ አፍሪካ እንደሆነ የሚነገርለት ቢጫ ወባን መቋቋም አልቻሉም። ይሄኔ ነው ናፖሌዎን ሄይቲን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቅኝ ሊገዛቸው ያሰባቸውን አገራት ጥሎ የወጣው።

የፈረንሳዩ መሪ 2.1 ሚሊዮን ስኩዌር መሬት ከሄይቲ ቆርሶ ለዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት መሸጡ አይዘነጋም። ይህ በታሪክ የሉዊዚያና ሽያጭ ተብሎ ይታወቃል።

አፍሪካ ሪንደርፔስትና ቅኝ ግዛት

የቁም እንስሳትን የፈጀው ሪንደርፔስት የተሰኘው በሽታ አውሮፓውያን የአፍሪካ አገራትን በቅኝ ግዛት እንዲቀራመቱ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

ከ1888 እስከ 1897 ባለው ጊዜ የተከሰተው ይህ እንስሳትን የሚያጠቃ ቫይረስ 90 በመቶ የአፍሪካ ከብቶችን እንደፈጀ ይነገራል። በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ፣ በምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ያሉ አርብቶ አደሮች በዚህ ሳቢያ እጅግ ተጎድተዋል።

ይህ እንስሳትን የሚያጠቃ ቫይረስ በርካቶች እንዲራቡና እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል። አርብቶ አደሮች ብቻ ሳይሆኑ አርሶ አደሮችም ጭምር በዚህ ሳቢያ ተጎድተዋል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አፍሪካን ለመውረር የመጡት የአውሮፓ ቅን ገዢዎች ወረርሽኙ አላማቸውን ምቹ አደረገላቸው። በ1870ዎቹ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ስር የነበረው የአፍሪካ አካል 10 በመቶው ብቻ ነበር።

ነገር ግን በወረርሽኙ ሳቢያ የአፍሪካ አገራት አቅም በመዳከሙ በ1900 ዘጠና በመቶ የአፍሪካ መሬት በቅኝ ገዥዎች እጅ እንዲሆን አድርጓል።

ወረርሽኝ የጣለው የቻይናው ሚንግ ስርወ መንግሥት

የሚንግ ስርወ መንግሥት ቻይናን ለሦስት ክፍለ ዘመናት አስተዳድሯል። ይህ አገዛዝ በቻይና ብቻ ሳይሆን በበርካታ የምሥራቅ እስያ አገራት ዘንድ የተንሰራፋ ነበር።

ነገር ግን የዚህ አገዛዝ ጨረሻ ያማረ አልነበረም። በ1641 በሰሜናዊ ቻይና ወረርሽኝ ተከሰተ። ይህ ወረርሽኝ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ችግሩን የከፋ ያደረገው ደግሞ በወቅቱ ተከስቶ የነበረው ድርቅና የአንበጣ ወረራ ነው።

ሰዎች የሚበሉት በማታጣቸው የሞተ ሰው ስጋ ሁሉ እስከ መ፥ብላት ደርሰው እንደነበር ይነገራል።

የቡቦኒክና የወባ በሽታ ቅልቅል ነው የሚባልለት ይህ ወረርሽን ያመጡት የሚንግ አገዛዝ መጣል የፈለጉት ቀጥሎ ወደ አገዛዝ የመጡት የኩዊንግ ስርወ መንግሥት ሰዎች እንደሆኑ ይነገራል። ያሰቡት ተሳክቶላቸውም ግዙፉን ሥርዓት ጥለውታል።

እነዚህ በታሪክ የተመዘገቡና የዓለምን ታሪክ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የቀየሩ ወረርሽኞች ናቸው። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝስ ታሪክ ይቀይር ይሆን?