ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተደናቀፈው ጣናን ከእምቦጭ የማጽዳት ሥራ
የኮሮናቫይረስ ከተከሰተና የሰዎች እንቅስቃሴ በእጅጉ ከተገታ በኋላ የጣና ሐይቅን ህልውና ስጋት ላይ የጣለውን የእምቦጭ አረምን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እንዲቀዛቀዝ ማድረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በወረርሽኙ ምክንያት በሐይቁ ላይ እየተንሰራፋ ያለውን አደገኛ አረም በተቻለ መጠን ለማስወገድ ከዚህ ቀደም ይወጣ የነበረው ሰው አሁን የለም ያሉን የአካባቢው አርሶ አደር አቶ ጎባው ደመቀ "የሕዝብ ተሳትፎ ቆሟል" ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸውልናል።
አሁን አረሙን በማስወገድ በኩል በክፍያ ከሚሰሩ ሰዎች በስተቀር በበጎ ፈቃደኝነት የሚያግዙ ሰዎች እየተሳተፉ አይደለም በተጨማሪም ዝናብ በመጀመሩ ምክንያት ሕብረተሰቡ ወደ ግል የእርሻ ሥራው እየተመለሰ ነው መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህ ምክንያትም በሐይቁ ላይ እየተንሰራፋ ያለው የእምቦጭ አረም እየጨመረና ይዞታውን እያሰፋ መሆኑን ይገልጻሉ።
ባለፉት 15 ዓመታት በጣና ሃይቅ ላይ በዓሳ ማስገር እና ንግድ ላይ የተሰማራው ብርሃኑ ውብነህ እንዳለው ደግሞ በአምስት ወረዳዎች በሚገኙ 27 ቀበሌዎች "የሐይቁን ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ተከትሎ ከጎርጎራ እስከ ጣና ጊዮርጊስ ያለው ዳርቻ ላይ እምቦጩ ሰፊ ሽፋን አለው።"
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጎንደር ዙሪያ ወረዳ የገጠር መሬትና አጠቃቀም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አድኖ አስማረ በበኩላቸው በወረዳው በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ከነበረው አንጻር አረሙ መጨመሩን ነግረውናል።
አረሙን ለማስወገድ በቀበሌዎቹ በሚገኙ ነዋሪዎች ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው እስከ የካቲት ድረስ በኅብረተሰቡ ጉልበት ሲሠራ ቢቆይም ካለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንጻር ይህንን መቀጠል አልተቻለም ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አረሙን በሰው ጉልበት ለማስወገድ እየተደረገ በነበረው ጥረት ላይ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው "የዚህን ዓመት ዕቅድ ማሳካት አልቻልንም። በሐይቁ ላይ ያለው የአረሙ ሽፋንም ጨምሯል" ብለዋል።
የጣና ሐይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው አረሙ ካለባቸው ሰባት ወረዳዎች በአምስቱ ቢታረምም ሥራው አለመቀጠሉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"የአረሙ ሁኔታ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ነው የሚባለውን ግን ትክክል አይደልም" ሲሉ አጣጥለውታል። "ከዚህ በፊት ከነበረው ቢያንስ እንጂ አይበዛም" ሲሉም አክለዋል።
"ከየካቲት በኋላ ዕቅዳችን ተበላሽቷል" ያሉት አያሌው (ዶ/ር) "እስከ ጥር ድረስ በነጻ ተሠርቷል። ከጥር እስከ ሰኔ ወጣቶችን አደራጅተን በመጠነኛ ክፍያ እንሠራለን ያለነው ንክኪ ስላለው ቋሞል" ብለዋል።
እምቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ ያደረሰውን ጉዳት "በቃላት መግለጽ ከባድ ነው" የሚለው ብርሃኑ አረሙ የሐይቁን ብዝሐ ህይወት ከመጉዳት ባለፈ በዓሣ ምርት፣ በመጠጥ ውሃ እና እርሻ ላይም ተዕጽኖ መፍጠሩን ይናገራል።
አቶ ጎባው በበኩላቸው መንግሥት፣ ወጣቱ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ በመቀናጀት "በክፍያም ቢሆን እየተሠራ በየጊዜው እንዲቀንስ ቢደረግ" የሚል ሃሳብ አላቸው።
ከሰባቱ ወረዳዎች በአምስቱ ውስጥ አረሙ ታርሞ መቃጠል ደረጃ ላይ ሲደርስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በመከሰቱ ምክንያት የማረሙ ሥራ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጻራሪ የሰዎች በጋራ መሰባሰብ እና ንክኪ ስላለው አማራጭ እየፈለግን ነው ብለዋል አያሌው (ዶ/ር)።
ትራክተር እና ጥቂት ሰዎችን በማቀናጀት አረሙን ለመሳብ በማሰብ 10 ትራክተሮች ሥራ የመጀመሩ ሲሆን በተጨማሪም አነስተኛ የኪስ ገንዘብ በመስጠት በቤተሰብ ደረጃ መታረም ያለበት ተለክቶ እየተሰጠ እንዲታረም ለማድረግ እየታሰበ መሆኑንም አስረድተዋል።
እንደማሽን፣ ኬሚካል እና ጢንዚዛ ያሉ አረሙን ሊያጠፉ ይችላሉ የተባሉ አማራጮችን መጠቀምን በተመለከተ "ዕቅዳችን አዋጪ የሆነውንና ጉዳት የማያደርሱትን አማራጮች ሁሉንም በማቀናጀት ጥቅም ላይ አውሎ አረሙን ማጥፋት ነው" ያሉትዋና ሥራ አስኪያጁ በዚህ ዓመት አምስት ዘዴዎችን መሞከራቸውን አስታውቀዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ቢደናቀፍም ዋነኛው ዘዴ የሰው ጉልበት መሆኑን ጠቅሰው ከተሞከሩት ዘዴዎች "የተሻለው በትራክተር አማካይነት የሚጎተተው ነው" ብለዋል ዋና ሥራ አስኪያጁ።
"ዘንድሮ ችግሮችን በደንብ በመለየት ለሚቀጥለው ዓመት ጥሩ እንሠራለን" ሲሉም ለቀጣይ ዓመት ያለቸውን ተስፋ ገልጸዋል።