ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአይኤሱ ቀጣናዊ መሪ ሼኽ ኮራሳኒ አፍጋኒስታን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ
ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) የተሰኘው ቡድን የደቡብ እስያና የሩቅ ምሥራቅ መሪ ካቡል ውስጥ መያዙን የአፍጋኒስታን የስለላ ሰዎች ተናግረዋል።
ዚያ ኡል-ሃቅ ወይም ሼኽ ኦማር ኮራሳኒ በሰተሰኘ ስሙ የሚታወቀው ግሰለብ ከሌሎች ሁለት ነባር መሪዎች ጋር ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።
ምንም እንኳ አፍጋኒስታን ውስጥ ዋነኛው ታጣቂ ቡድን ታሊባን ቢሆንም አይኤስ በተወሰኑ ቦታዎች እንቅስቃሴ ከማድረግም በላይ ካቡል ውስጥ የቦንብ ጥቃቶችን ፈፅሟል።
የደኅንነት ሰዎች የሰውየው በቁጥጥር ሥር መዋል ትልቅ ድል ነው ይላሉ።
ከቡድኑ መሪ ጋር የተያዙት ሌሎቹ ሁለት ግለሰቦች ቃል አቀባዩ ሳሂብና የደኅንነት ኃላፊው አቡ አሊ ናቸው ተብሏል።
የአፍጋኒስታን ስለላ ተቋም ባወጣው መግለጫ 'ኦፕሬሽኑ' የተሳካ ሊሆን የቻለው ከዚህ ቀደም ከተያዙ የአይኤስ አባላት በተገኘ መረጃና ክትትል ነው።
መግለጫው አክሎም አምስት የቡድኑ አባላት መገደላቸውንና ስምንት ደግሞ መቁሰላቸውን አትቷል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው መግለጫው "ሌሎች የቡድኑ መሪዎችንም አድነን ለመያዝና ለማንበርከክ እንቅስቃሴያችንን እንቀጥላለን" ይላል።
አይኤስ የተሰኘው ቡድን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አፍጋኒስታን ውስጥ በርካታ የቦንብ ጥቃቶችን ፈፅሟል። ዋነኛ ዒላማው ደግሞ የሺአ ሙስሊም አፍጋናውያንና አናሳ ጎሳዎች ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ዓመት ያገኘው አንድ መረጃ እንደሚናገረው ሼኽ ኮራሳኒ ባሳየው ደካማ ውሳኔ በሌላ ሰው ተተክቷል። መረጃውን ማረጋገጥ ግን አልተቻለም።
ምንም እንኳ ዩናይትድ ስቴትስ እና ታሊባን ወታደሮቻቸውን ከጦርነቱ ቀጣና ለማስወጣት ከስምምነት ቢደርሱም አፍጋኒስታን አሁንም በነውጥ መታመሷን ቀጥላለች።
ከአይኤስ ጋር የቅርፅም የዓላማም ምስስል የለኝም የሚለው ታሊባን ከስምምነቱ በኋላ የሚያደርሳቸውን ጥቃቶች ቀንሷል።