ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአቶ በረከት ስምኦን እና ታደሠ ካሣ ላይ የፍርድ ውሳኔ ተላለፈ
በእነ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሠ ካሣ ላይ የፍርድ ውሳኔ ተላለፈ።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት በቀድሞ ባለስልጣናቱ በአቶ በረከት ስምኦን ላይ ስድስት ዓመት እንዲሁም በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የስምንት ዓመት የእስር ውሳኔ አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ የከሳሽንና የተከሳሾችን ክርክር ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ዛሬ በዋለው ችሎት በ1ኛ እና 2ኛ የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በተባሉት በ1ኛ ተከሳሽ አቶ በረከት ስምኦን ላይ የስድስት ዓመት እስር እና የ10 ሺህ ብር የቅጣ ውሳኔ አስተላልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በተባሉት 2ኛ ተከሳሽ አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ደግሞ የስምንት ዓመት የእስር ቅጣትና የ15 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ መበየኑን የአማራ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ችሎቱ ሁለቱ ግለሰቦች ይግባኝ የማለት መብት እንዳላቸው የገለጸ ሲሆን ችሎቱ ፍርዱ በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ይሰላልም ተብሏል።
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሠ ካሣ በጥረት ኮርፖሬሽንን በቦርድ ሰብሳቢነትና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሚናቸው ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥር 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ይታወሳል።
ከቀናት በፊት በሁለቱ የቀድሞ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።
አቶ በረከት ስምኦን ማናቸው?
አቶ በረከት ስምኦን ከኤርትራዊያን ቤተሰቦቻቸው ጎንደር ውስጥ ተወልደው እንዳደጉ ይነገራል። ቤተሰቦቻቸው ያወጡላቸው ስም መብራህቱ ሲሆን የአባታቸው ስም ደግሞ ገብረሕይወት እንደሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ።
በቀዳሚነት የታላቅ ወንድማቸውን ፈለግ በመከተል የኢህአፓ አባል ሆነው ወደ ትግሉ ከገቡ በኋላ የስም ለውጥ እንዳደረጉም እነዚሁ ሰዎች ያስታውሳሉ። ስማቸውን ለምን እንደለወጡ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም የሌላ ታጋይ ስም እንደወሰዱ ግን ይነገራል።
ይህም በረከት ስምኦን የሚባል የኢህአፓ ታጋይ እንደነበርና በትግሉ ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ከትግሉ ሜዳ ድንገት በመሰወሩ በርካታ የኢህአፓ አባላት የተገደለ መስሏቸው ነበር።
በነበረው ልምድም ይህን ታጋይ ለማስታወስ መብራህቱ ገብረህይወት በረስምኦን የሚለውን ሙሉ ስም እንደወሰዱም የቅርብ ሰዎቻቸው ያወሳሉ።
አቶ በረከት ከየት ወደየት?
አቶ በረከት ስምኦን ወደ ትግል የገቡት በመጀመሪያ የኢህአፓ አባል ሆነው ሲሆን ድርጅቱ በዋናነት ከደርግና ከሌሎች ተቀናቃኝ ድርጅቶች በገጠመው ጥቃት በተዳከመበት ወቅት በውስጡ የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ድርጅቱን ጥለው ወጡ።
ከኢህአፓ የተለዩት አቶ በረከት ከትግሉ ጠቅልለው ግን አልወጡም ከጓዶቻቸው ጋር ብዙም ያልቆየውን ኢትዮጵያ ኮሚኒስት ፓርቲ (ኢኮፓ) አቋቁመው የነበረ ሲሆን ቀጥለውም አሁን የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ የነበረው አማራ ዲሞክራቲክ ፓርቲ መነሻ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ኢህዴን) በመመሥረት ከህወሓት ጋር ግንባር ፈጥረው ደርግን ታግለዋል።
ከደርግ ውድቀት በኋላ አቶ በረከት በብአዴን ውስጥ ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ሰዎች መካከል ቀዳሚው በመሆን ቆይተዋል።
አቶ በረከት የነበሩባቸው ቁልፍ የመንግሥት ኃላፊነቶች
- የማስታወቂያ ሚኒስትር
- የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር
- የጠቅላይ ሚንስትሩ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪ ሚንስትር
- በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር
- የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀ መንበር