ኮሮናቫይረስ፡ በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት በርካታ አፍሪካውያን የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል

የዳሰሳ ጥናት ከተካሄደባቸው ከ20 የአፍሪካ አገራት ዜጎች መካከል ሁለት ሶስተኛው ለ14 ቀናት በቤት እንዲቆዩ ቢገደዱ በቀናት ልዩነት ምግብ እንጨርሳለን ያሉ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሆኑት ደግሞ ባዶ ኪሳቸውን እንደሚቀሩ ተናግረዋል።

የዳሰሳ ጥናቱን ያካሄደው የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል ሲሆን፤ የጥናቱ ውጤት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ወደፊት ምን አይነት ፖሊሶዎችን መቅረጽ እንዳለባቸው ጥቆማ ይሰጣል ተብሏል።

በሪፖርቱ መንግሥታት የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች የዜጎችን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘቡ ከሆኑ ግጭት እና አለመረጋጋት ሊከሰት እንደሚችል ተጠቁሟል።

ጥናቱ በ20 አገራት የሚገኙ 28 ከተሞች ላይ በመጋቢት ወር የተከናወነ ነው።

ሪፖርቱ በአንዳንድ አገራት ዜጎች በኮቪድ ምክንያት ከደረሰባቸው ጫና ለመላቀቅ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው አደባባይ መውጣታቸው፤ ሰዎች ምን አይነት ጫና ውስጥ እንዳሉ ያሳያል ይላል ሪፖርቱ።

ሪፖርቱ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲጥሉ በዜጎቻቸው ድጋፍ የተቸራቸው መንግሥታት ነበሩ ብሏል።

በዳሰሳ ጥናቱ የገቢ መጠናቸው አስተኛ የሆኑ ሰዎች፤ በቤት እንዲቀመጡ ቢታዘዙ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያስቀመጡትን ጥሪት እንደሚጨርሱ ተናግረዋል።

ጥናቱን ያካሄዱ ተመራማሪዎች መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከቤት አትውጡ ከማለታቸው በፊት እነዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን እንዳስገደዳቸው ወቅታዊ እና በቂ የሆነ መረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ፣ በበሽታው ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለመለየት እና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም የጤና ስርዓቱን ማሻሻል ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ምክር ሰጥተዋል።

በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 48 ሺህ 22 የደረሰ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 16ሺህ 19 አገግመዋል፣ 1ሺህ 878 ቱ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።