ፖሊስ በመምሰል በፈረንሳይ ሰዎችን ሲያጭበረብሩ የነበሩ የተባሉ ኢራናውያን በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፖሊስ በመምሰል በፈረንሳይ ሰዎችን ሲያጭበረብሩ የነበሩ የተባሉ ኢራናውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነገረ።
አንዲት ሴት እና ሦስት ወንዶች ፖሊስ በመምሰል የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት ሰዎች ከቤታቸው ለመውጣት ምክንያታቸው የተዘረዘረበትን ወረቀት እንዲያሳዩ ሲጠየቁ ነበር።
አራቱ አጭበርባሪዎች እስከ 25 ሺህ ዩሮ (27 ሺህ ዶላር) ሳያጭበረብሩ አይቀርም ተብሏል።
ላለፉት 7 ሳምንታት ፈረንሳይዊያን ከቤት መውጣት የሚችሉት ወደ ሥራ ለመሄድ፣ ምግብ ለመሸመት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ወይም አስቸኳይ የቤተሰብ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው ብቻ ነው።
ከቤት ውጪ በሚገኙበት ወቅት ዜጎች ከቤት የወጡበትን ምክንያት የሚያትት ወረቀት መያዝ ይኖርባቸዋል።
ፖሊስ እንዳለው እነዚህ አራት አጭበርባሪዎች የፖሊስ ዩኒፎርም እና የአፍ እና የአፍንጫ ጭምብል አጥልቀው ሰዎችን በሁኔታቸው እየለዩ ያስቆማሉ። ከዚያም ከቤት የወጡበትን ምክንያት የሚያስረዳ ወረቀት እየጠየቁ የሰዎችን ኪስ እና ቦርሳ በመበርበር ያገኙትን ጥሬ ገንዘብም ይሁን ወድ ንብረት ሲዘርፉ ቆይተዋል።
ፖሊስ ኮሚሽነሩ ናታን ባዎር እንዳሉት አራቱ ኢራናውያን "ጥሩ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች አይደሉም" ትኩረት ሲያደርጉ የነበሩትም ስደተኞች ላይ ነው።
ኮሚሽነሩ ጨምረው እንዳሉት በአጭበርባሪዎች ከተታለሉ ሰዎች መካከል 7 ሰዎችን ለይተዋል። ከእነዚህም መካከል ከአንዱ 12 ሺህ ዩሮ ተዘርፏል።














