ኮሮናቫይረስ: ትራምፕ ቫይረሱ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበትን ጊዜ አልፏል አሉ

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱ በአሜሪካ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት ጣሪያን ማለፉን እና አንዳንድ ግዛቶች በዚህ ወር መከፈት እንደሚጀምሩ ተናገሩ።

ትራምፕ ቫይረሱን በማስመልከት በዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ከአሜሪካ ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ግዛቶቹ ስለሚከፈቱበት ሁኔታ ዛሬ ምሽት መግለጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

"አሃዞች እንደሚያሳዩት በመላው አገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው" በማለት ትራምፕ ተናግረዋል።

አሜሪካ 638,000 ዜጎቿ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ30,800 በላይ ነው።

ከሌሎች አገራት በላይ በአሜሪካ በቫይረሱ የሞቱ እና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ለምን ከፍ አለ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዝደንቱ ሲመልሱ፤ "እንዳንድ አገራት የሚያወጡትን አሃዝ የሚያምን አለ?" በማለት የቻይናን ስም ጠቅሰዋል።

ትራምፕ ጨምረውም ቫይረሱ በቻይዋ ዉሃን ከተማ ሳይሆን ከዉሃን ላብራቶሪ ነው የወጣው ስለሚባለው ያልተረጋገጠ ሪፖርት አሜሪካ ትመለከተዋለች ብለዋል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በቤጂንግ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዉሃን በሚገኙ ሁለት ላብራቶሪዎች የደህንነት ጉዳይ ያሳስበናል ሲል ሪፖርት ስለማድረጉ ዘግበዋል።