ኮሮናቫይረስ፡ ኦፕራህ ዊንፍሬይ ኮሮናቫይረስ በጥቁሮች መጨከኑ እየረበሻት እንደሆ ተናገረች

ኦፕራህ ዊንፍሬይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዝነኛዋ የቴሌቪዥን ትዕይንት አሰናጅ ኦፕራህ ዊንፍሬይ ጥቁሮች የኮሮናቫይረስን በዋዛ እንዳይመለከቱት አሳስባለች።

"ይህ ክፉ ደዌ በጥቁሮች ላይ ክንዱ በርትቷል፤ ጥቁሮች ደግሞ ተዘናግተናል፤ ይህን መቀየር አለብን" ብላለች ኦፕራህ።

በርካታ ዜጎችን እያሳጣት ባለችው የዓለም ኃያሏ አገር አሜሪካ ከነጮች ይልቅ ጥቁሮች በቫይረሱ መጎዳታቸውን በተከታታይ የወጡ አሃዛዊ መረጃዎች አሳይተዋል።

በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን ካለፈ ሰነባብቷል። የሟቾች ቁጥርም በቅርብ ቀናት 30 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል።

በሕዝብ ብዛት በዓለም ሦስተኛዋ አገር አሜሪካ ውስጥ የአፍሪካ አሜሪካዊያን ብዛት 13 ከመቶ ብቻ ነው። ሆኖም በዚህ ቫይረስ የተጠቁ አፍሪካ-አሜሪካውያን ድርሻ ግን ከ33 ከመቶ በላይ ነው። ይህ ለብዙ የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች ግራ ነው።

ይህ አሃዝ ይበልጥ አስደንጋጭ የሚሆነው ወደ አንዳንድ የአሜሪካ ከተሞች ሲወርድ ነው።

ለምሳሌ ቺካጎ ውስጥ የጥቁር አሜሪካዊያን ብዛት ከአጠቃላዩ ሕዝብ 23 ከመቶ ቢሆንም በቫይረሱ ከሞቱት 70 ከመቶዎቹ እነርሱ መሆናቸው ዶናልድ ትራምፕን ጭምር ያስገረመ ሀቅ ሆኗል።

ኦፕራህ እንደምትለው ስለ ኮቪድ-19 መጀመሪያ የተሰጠው መረጃ ለጥቁር አሜሪካዊያን በሚሆን መልኩ አልተዘጋጀም።

ኦፕራይ ከሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራት ቆይታ ይህንኑ አብራርታለች።

"ቻይና ዉሃን ከተማ ወረርሽኙ ሲከሰት ሰምተን የሩቅ ነገር ሆኖ ተሰማን። በሚልዋኪ ከጥቁር አሜሪካዊያን ጋር ሳወራ ወረርሽኙ ዋሽንግተን ደርሷል ስንል እሱም ሩቅ ተደርጎ ታሰበ። 'በዋሺንግተን ስለ ኮቪድ-19 ሰምተናል፤ ከእኛ ጋር ምን አገናኘው፤ ሩቅ ነው" ሲሉኝ ነበር ብላለች ኦፕራህ።

"መዘንጋት የሌለብን ጥቁር አሜሪካዊያን በአስምና በስኳር በሽታዎች ከነጮች ይበልጥ የተጠቃን ስለሆነ ቫይረሱ ከሁሉም በላይ በእኛ ላይ እንደሚበረታ ነው" በማለት ያደረባትን ስጋት አጋርታለች።

በሳምባ ምች ህመም ባለፈው ዓመት ተጠቅታ የነበረችው ኦፕራ ዊንፍሬይ በግሏ በኮሮናቫይረስ ላለመያዝ ከፍ ያለ ጥንቃቄ እያደረገች እንደሆነ ተናግራለች።

በተለይም ምንም ምልክት የማያሳዩ የቫይረሱ ተያዦች ከባድ ስጋት እንደደቀኑ አብራርታለች።

ምልክት የማያሳዩ ሰዎችን በተመለከተ ከእርሷ ጋር ስለ ኮቪድ-19 በቴሌቪዥን መሰናዶዋ ላይ ቆይታ አድርጎ የነበረው ዝነኛው ተዋናይ ኢድሪስ ኢልባ ራሱ ሲመረመር ቫይረሱ እንደተገኘበት ጠቅሳ፤ ሆኖም ኢድሪስ ኢልባ ባይመረመር ኖሮ ምንም አይነት ምልክት ስለማያሳይ በሽታው እንዳለበት ማወቅ አይችልም ነበር ብላለች።

በአሜሪካ ለምን ጥቁሮች ከነጮች የበለጠ በቫይረሱ ተጠቂ ሆኑ ለሚለው ምላሽ ለማግኘት ሰፊ ጥናት እየተደረገ ሲሆን ቅድመ ጥናቶች እንዳመላከቱት ከሆነ ግን አብዛኛዎቹ ጥቁር አሜሪካዊያን ቅጥ ባጣ ውፍረት፣ የስኳር፣ የአስምና የደም ግፊት ታማሚዎች መሆናቸው፣ በዝቅተኛ ገቢ ሥራዎች ላይ በስፋት በመሰማራታቸው ተጋላጭነታቸውን ስለሚጨምረው እንደሆነ ተደርሶበታል።

እንዲሁም የጥቁር አሜሪካዊያን የአኗኗር ዘይቤያቸው ጥግግት የሚበዛው መሆኑ እንደ አንድ ምክንያት ተወስዷል። ለጤና አቅርቦት የራቁ መሆናቸውም ሌላው ሰበብ ነው።

ከዚህም ባሻገር ወረርሽኙ የጀመረ ሰሞን ቫይረሱ ጥቁር አይዳፈርም የሚል ሰፊ የተሳሳተ መረጃ በጥቁር አሜሪካዊያን ዘንድ ተዛምቶ ነበር። ይህም ከፍ ያለ መዘናጋትን ፈጥሮ እንደነበር ይነገራል።

ባለፈው ሳምንት ዝነኛው የቀድሞ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማጂክ ጆንሰን በሲኤንኤን ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ እንደመሰከረው ኮቪድ-19 ጥቁሮችን አይቋቋምም የሚል እምነት በስፋት በአፍሪካ-አሜሪካዊያን መካከል ተንጸባቆ ነበር ብሏል።

"ከ30 ዓመታት በፊት እንደነበረው ነው፤ ጥቁሮች ኤችአይቪ ኤድስ አይዛቸውም፤ ኤድስ የነጭ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ፈጻሚዎች በሽታ ነው ይባል ነበር፤ አሁንም ደግመን ልንሳሳት አይገባም" ብሏል ማጂክ ጆንሰን።

ኮሮና
Banner