ኮሮና ቫይረስ፡ የዓለም ባንክ ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገራት ኢኮኖሚያዊ ድቀት እንደሚያጋጥማቸው ተነበየ

የዓለም ባንክ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከግማሽ ምዕተዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 ምክንያት የኢኮኖሚ ድቀት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተነበየ።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት በዚህ ዓመት ብቻ በ2.1 በመቶ የሚጎዳ ሲሆን ይህ ጉዳት እስከ 5.1 ድረስ ሊደርስ ይችላል ብሏል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በ52 የአፍሪካ አገሮች የተከሰተ ሲሆን እስካሁን ድረስ በመላ አህጉሪቱ 10,250 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችም ቁጥርም 492 ደርሷል።

የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ አበዳሪ አገራት ለአፍሪካ እዳቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንዲያራዝሙ እና አገራት ያላቸው ገንዘብ ወደ ሕይወት ማዳንና ኑሮን ማሻሻል ላይ ማዋል እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አፍሪካ በኮቪድ-19 ከተጠቁ አህጉራት የመጨረሻዋ ስትሆን፣ አገራት ድንበራቸውን መዝጋት፣ ዜጎቻቸው ከቤት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፣ መንገደኞችን በለይቶ ማቆያ ማስቀመጥ ርምጃዎችን የወሰዱት በፍጥነት ነበር።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመጀመሪያው ጉዳት ንግድን ማስተጓጎል ነበር። የዓለም ባንክ እንደሚለው ከሆነ የግብርና ምርቶች አቅርቦት መቀነስ፣ የአቅርቦት መስተጓጎል፣ እና የሕይወት መጥፋት ወደ ምግብ እጥረት ሊመራ ይችላል።

በአፍሪካ በምጣኔ ሃብታቸው ግዙፍ የሆኑት ናይጄሪያና አንጎላ በወረርሽኙ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መውረድ ምጣኔ ሃብታቸው ክፉኛ ከተጎዳ አገራት መካከል ይገኙበታል። ደቡብ አፍሪካም ብትሆን የማዕድን ገቢዋ አሽቆልቁሏል።

ከኢትዮጵያና ኬንያ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ሁሉም ተዘግተዋል። ከባህርማዶ ወደ አገር ውስጥ ይደረግ የነበረው የጎብኚዎች ፍሰት፣ የሚላክ የውጪ ምንዛሪ፣ እንዲሁም የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቆሟል።

በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ እንዲሁም በደቡባዊ አፍሪካ ያለው ድርቅ በአፍሪካ ያለውን ችግር ተደራራቢ አድርጎታል።

የዓለም ባንክ ብድር መክፈል ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም የሚል ምክረ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህም በዓመት ለብድር ክፍያ የሚውለውን ወደ 35 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ለወለድ ክፍያ የሚውለውን 44 ቢሊየን ዶላር ነፃ ያደርጋል ተብሏል።

ድርጅቱ አክሎም የአፍሪካ አገራት ለድሃ ዜጎቻቸው ምግብ እንዲያከፋፍሉ፣ መሰረታዊ ግልጋሎቶች ላይ የተጣሉ ክፍያዎችን እንዲያነሱ መክሯል።