ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የአሜሪካዋ ግዛት ዊስኮንሰን አስገዳጁን ቤት የመቀመጥ ሕግ ተላልፋ ምርጫ አካሄደች
በኮሮናቫይረስ በርካታ ዜጎቿን እያጣች ባለችው አሜሪካ በበርካታ ግዛቶች ቤት የመቀመጥ አስገዳጅ ሕግ ቢወሰንም የዊስኮንሰን ግዛት ይህንን ተላልፋ በትናንትናው እለት ምርጫ አካሂዳለች።
ጥቂት ቁጥር ባላቸው የምርጫ ጣቢያዎችም በርካታ ሰዎች ተሰልፈው ታይተዋል። የምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችም ኦክስጅን መተላለፊያ ያለው ከእግር እስከ ጭንቅላት የሚሸፍን አልባሳት ለብሰው ታይተዋል።
የዊስኮንሰን አስተዳዳሪ ምርጫውን ወደ ሰኔ ለማስተላለፍ አቅደው የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንን ውሳኔ ሽሮ ምርጫው መካሄድ አለበት ብሏል።
ቀጣዩ የዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው ለመወዳዳር እየተፋለሙ ያሉት ጆ ባይደንና በርኒ ሳንደርስን አሸናፊ ለመለየት ከተደረጉ የመጀመሪያ ዙር ምርጫዎችም አንዱ ነው።
የዚህ ምርጫ አሸናፊም በፈረንጆቹ ህዳር ለተያዘው ምርጫ ከሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚወዳደር ይሆናል።
የአካባቢው ምርጫ አስፈፃሚዎችም በምርጫው ወቅት እንዲሁም በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ተገኝተዋል።
አሜሪካ ለሦስት ሳምንታት ያህል ቤት መቀመጥ እንዲሁም እንቅስቃሴ የሚገድብ መመሪያ ብታወጣም ዊስኮንሰን ይህንን ሕግ ተላልፋ ምርጫ ስታካሂድ የመጀመሪያዋ ግዛት ሆናለች።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመጠቃት አለምን እየመራች ባለችው አሜሪካ አራት መቶ ሺህ የሚጠጋ ሰው በቫይረሱ ተይዟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አገሪቷ እንዲህ ባለ የጤና ቀውስ ባለችበት ሰዓት ምርጫ መካሄዱ ተተችቷል።
ሌሎች ግዛቶች ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመውታል።
እስካሁን ባለው መረጃ በዊስኮንሰን ግዛት 2 ሺህ 500 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 92 ግለሰቦች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።