ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የኮሮናቫይረስ መነሻ የነበረችው የቻይናዋ ዉሃን ከተማ በከፊል ለእንቅስቃሴ ክፍት ሆነች
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የጀመረባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ለሁለት ወር ያህል ከእንቅስቃሴ ታግዳ ከቆየች በኋላ በከፊል ክፍት ሆነች።
ዛሬ በርካታ መንገደኞች በዉሃን ባቡር ጣቢያ ሲተራመሱ ታይተዋል። ከስፍራው እንደሚወጡት ዘገባዎች ከሆነ ሰዎች ወደ ዉሃን ከተማ መግባት ቢፈቀድላቸውም መውጣት ግን አልተፈቀደም።
የሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ዉሃን ከ50 ሺህ በላይ ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎች የተገኙባት ሲሆን 3 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
እንደ ቻይና መንግሥት መረጃ ከሆነ በግዛቲቱ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየቀነሰ ነው።
ግዛቲቱ ቅዳሜ ዕለት 54 ሰዎች ብቻ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የገለፀች ሲሆን ሁሉም ሕሙማን ከሌላ አካባቢ የመጡ ናቸው ተብሏል።
ቻይና በአሁኑ ሰዓት ከሌላ አካቢቢ የሚመጡ ህሙማንን ለመከላከል በሚል የመኖሪያ ፈቃድም ሆነ ቪዛ የያላቸው መንገደኞች ቢሆኑ እንኳ ከአገር ውጪ የሚመጡ የማንኛውንም አገር ዜጎች እንዳይገቡ አግዳለች።
የቻይናንም ሆነ የሌላ አገራትን በረራ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እንዲሆን በተጨማሪም አውሮፕላኑ ካሉት መቀመጫዎች 75 በመቶውን ብቻ መንገደኞች መያዝ እንደሚችል አስታውቃለች።
የኮቪድ-19 ቫይረስ በቻይናዋ ዉሃን የባህር አሳ ምግቦች በሚሸጥበት ገበያ እንደጀመረ የሚገመት ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው "ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ ላይ በተሰማሩ ሰዎች አማካኝነት ነው" ተብሏል።
በከተማዋ የሚኖሩ 11 ሚሊየን ሰዎች በቤታቸው ተቀምጠው ያሳለፉ ሲሆን ከከተማዋ የሚያስወጡ የተለያዩ መንገዶችም ተዘግተው ነበር።
ነገር ግን ከአርብ ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች ለእንቅስቃሴ ክፍት መሆናቸው ታውቋል። የከተማዋ 17 የባቡር መንገዶችም ቢሆኑ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
ማንኛውም ዉሃን የሚደርስ መንገደኛ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ላይ ጤነኛ መሆኑን የሚያሳይ በመተግበሪያ ላይ የተጫነለትን አረንጓዴ ምልክት ማሳየት ይጠበቅበታል።
ከዉሃን መውጣት የሚፈቀደው የአገር ውስጥ በረራ ሲጀምር ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሆነ የከተማዋ ባለስልጣናት ገልፀዋል።
በቻይና ባለፈው ሕዳር ወር ላይ ወረርሽኙ የጀመረ ሲሆን በዚህም የተነሳ 3300 ሰዎች ሞተዋል። ከዚያ በኋላ ወረርሽኙ የተስፋፋባቸው ጣሊያንና ስፔን ግን ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር አስመዝግበዋል።