በአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ዳኞች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በዳኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እየተበራከተ መምጣቱ ተገለጸ።
ይህ ጥቃት በተለያዩ የክልሉ የፍትሕ መዋቅር ውስጥ በመሆን ሕግን እንዲተረጉሙ በተመደቡ ዳኞች ላይ እየተፈጸመ መሆኑን ዳኞችና የክልሉ ፍትህ ቢሮ አመልክቷል።
የክልሉ መንግሥትም ይህንን ድርጊት በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርማጃ ለመውሰድ ምርመራ እኣካሄደ መሆኑንም አመልክቷል።
በቅርቡም የወረዳ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ዳኛ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ኪዳኔና ባልደረቦቻቸው ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። አቶ ኤፍሬም ከሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር አረፍ ብለው ስለ ውሏቸው እና ሥራቸው እየተጫወቱ ነው።
"የካቲት 18 ከሥራ በኋላ ቤተክርስቲያን ጸሎት አድርገን አረፍ ብለን ነበር" ሲሉ ዕለቱን ያስታውሳሉ።
ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ ነበር መምጣታቸውን ያላስተዋሏቸው ግለሰቦች ከኋላ ደርሰው ጥቃት ያደርሱባቸው የጀመሩት። ጥቃት አድራሾቹ ሁለት መሆናቸውን ይገልጻሉ።
"ከፍተኛ ጉዳት ነው" ይላሉ አቶ ኤፍሬም "በተለይ አንደኛው ዳኛ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰበት። የዱላ ድብደባ ነው። እኔን ማጅራቴ አካባቢ ነው የመቱኝ። ሌላውን ጓደኛዬን ራሱን ነው የመቱት። ሦስተኛው ጥርሱ ረግፏል፤ ዓይኑ አካባቢ ጉዳት ደርሶበታል፤ አፍንጫውም ተሰብሯል። በጣም ዘግናኝ ጉዳት ነው የደረሰበት" ሲሉ የጉዳቱን መጠን ያስረዳሉ።
አቶ ኤፍሬም ጥቃት አድራሾችንም ሆነ ምክንያታቸውን እንደማያውቁ ነው ለቢቢሲ የገለጹት። ባሉበት ድንገተኛ የሆነ ጥቃት እንደደረሰባቸው እንጂ ከጥቃቱ ጀርባ ስላለው ሁኔታ መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ጥቃቱ የደረሰባቸው ከሥራቸው ጋር ተያያዥ በሆነ ምክንያት እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "ከሥራ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? ጸብ የለንም። ከሥራችን ውጭ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ከማንም ጋር ግላዊ ጸብ የለንም። ለዚህ ሊያደረስ የሚችል ነገር የለንም። መቶ በመቶ ባይባልም በሥራችን ምክንያት ነው ሊባል ነው የሚችለው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጥቃቱን "አስነዋሪ፣ አሳዛኝ እና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ ናቸው።
"በዱላ እና በድንጋይ ነው ጠጥቃቱ የተፈጸመው። ተዘናግተው በተቀመጡበት ከኋላ መጥተው ነው ያጠቋቸው። ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበት ሁኔታም አልነበረም" ሲሉ ያስረዳሉ።
"ዳኞች የድርብ ችግር ሰለባ ሆነዋል" የሚሉት አቶ ታዘባቸው፤ "ውስብስብ መዝገቦችን በአግባቡ ለመወሰን ቀን ከሌት ከመሥራታቸውም ሌላ ሕገ ወጦች ጥቃት እያደረሱባቸው ነው" ይላሉ።
"በርካታ ዳኞች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። ስለሆነም በቀላሉ መታየት የለበትም። እልባት ማግኘት አለበት። ጥቃቱም መታየት እና መፈተሽ አለበት።"
ይህ ጥቃትም የመጀመሪያ አለመሆኑን ጠቁመው ሁኔታውም ዳኞችን ተስፋ እስከማስቆረጥ እንደደረሰ ገልጸዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ይህን ምክንያት አድርጎ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
የክልሉ ዳኞች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር ያለማንም ተጽዕኖ በሕግ ብቻ ውሳኔ በመስጠት የዳኝነት አገልግሎቱ ላቅ እንዲል እየሠሩ መሆኑን በመግለጫው ተመልክቷል።
በተለያዩ ወቅቶች በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በአዊ ብሔረሰብ፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ ዳኞች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እና ተፅዕኖዎች መድረሳቸውን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
"ጥቃቱ በተመታው ዳኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በፍትህ ሥርዓቱና በሕዝቡ ላይ እንደደረሰ ታስቦ መንግሥት እና ኅብረተሰቡ ርብርብ በማድረግ ጥበቃ ሊያደረግላቸው ይገባል" የሚሉት አቶ ታዘባቸው፤ "በዚህ መልኩ ከተሄደ [የፍትህ] ሥርዓቱ ችግር ውስጥ ይወድቃል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ችግሩ በተደጋጋሚ የተከሰተው ሙሉ በሙሉ በቸልታ ስለታለፈ አይደለም ብለዋል።
"የደህንነት ጥበቃ የላቸውም። በየቀኑ ፍርድ ይሰጣሉ። የተፈረደበት ወገን ላይደሰት የሚችልበት ሁኔታ አለ። በየደረጃው ያሉ ዳኞች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። ራሳቸውን የሚከላከሉበት መሣሪያ የላቸውም።
"ጠባቂያችን ሕዝብ፣ ህሊናችንና ሥራችን ነው ባሉበት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። መንግሥት የደህንነት ጥበቃ ማድረግ አለበት። መሣሪያ ሰጥቶ ራሳቸውን እንዲከላከሉ በማድረግ ኃፊነቱን መወጣት አለበት" ሲሉ መፍትሔ ያሉትን አስቀምጠዋል።
በዚህ ሃሳብ ዳኛ ኤፍሬምም ይስማማሉ።
"ለዳኞች ጥበቃ ሊደረግ ይገባል ምክንያቱም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ነው ውሳኔ የሚሰጠው። መንግሥት በተለየ መንገድ ለዳኞች ጥበቃ ማድረግ አለበት። ትኩረት መሰጠት አለበት። ጉዳት አድራሾቹም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። በመንግሥት በኩል የዳኞች ጉዳይ ያን ያህል ትኩረት የሚሰጠው አይደለም።"
"ጥቃቱ በፍትህ ሥርዓቱም ሆነ በዳኞች ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ዳኞች ነጻ ሆነው ሕግን መሠረት አድርገው ውሳኔ እንዳይሰጡ ነው የሚያደርገው። መጀመሪያ የዳኞች ደህንነትና ህልውና ካልተረጋገጠ እንዴት ተብሎ ትክክለኛ የሆነ ፍትህ ሊሰጥ ይችላል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
ፍርድ ቤቶች መቶ በመቶ እንከን አልባ አለመሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ታዘባቸው፤ "ተበድለናል ወይም ፍርዱ ትክክል አይደለም ካሉ በይግባኝ መጠየቅ ይቻላል። የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ዳኞች ይኖራሉ። ዳኞች ላይ እርምጃ ይወሰዳል። እርምጃ የተወሰደባቸውም አሉ። የተባረሩ፣ የታሰሩም አሉ።"
አክለውም "ካልሆነ ግን የፍትህ ሥርዓቱን መጋፋት ነው። የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ ስለሆነ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና የጸጥታ አካላትም ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። ከአመራር እና የጸጥታ አካላት ጋር እንሠራለን። መንግሥት ልዩ ትኩረት ይሰጣል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።
ዱር ቤቴ ከተማ ጉዳት ከደረሰባቸው ሦስት ዳኞች መካከል ሁለቱ ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል። ሦስተኛው ግን ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ በህክምና ባለሙያዎች ርብርብ በማገገም ላይ ይገኛል።
ጉዳዩን ለማጣራት የምርመራ ቡድን ተቋቁሟል። "ቡድኑ እየሠራ ነው። የምርመራ ቡድኑ በራሱ መንገድ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ነው። በቅርቡ ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቀርባሉ ብለን እናስባለን" ሲሉ አቶ ታዘባቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሕግ እና ሥርዓት የማፍረስ ተግባርን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ፤ ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ እና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም አስታውቋል።












