ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊቷ ጠፈርተኛ አዲስ የህዋ ላይ ቆይታ ክብረ ወሰን አስመዘገበች
የናሳዋ ጠፈርተኛ ክርስቲና ኮች እስካሁን ወደ ህዋ በተደረገ ጉዞ ከዚህ ቀደም በሌላ ሴት የተያዘን ረጅሙን የበረራ ቆይታ በማጠናቀቅ የመጀመሪያዋ ሆናለች።
ክርስቲና ኮች ጉዞዋን ያደረገችበት የሩሲያዋ የህዋ መንኮራኩር ጉዞዋን አጠናቃ ካዛኪስታን ውስጥ ያረፈችው ዛሬ ነው።
ክርስቲና በዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ውስጥ 328 ቀናት በማሳለፍ ቀደም ሲል በአገሯ ልጅ ፔጊ ዋይትሰን ተይዞ የነበረውን የቆይታ ክብረ ወሰን ሰብራለች።
የክርስቲና ቆይታ እስካሁን በህዋ ጣቢያ ውስጥ በመቆየት ወደር አልተገኘለትም ከሚባለው ከወንዱ የስኮት ኬሊ ቆይታ በ12 ቀናት ብቻ ያነሰ እንደሆነ ተነግሯል።
መንኮራኮሩ ምድር ላይ ካረፈ በኋላ ለጋዜጠኞች ስላሻሻለችው የህዋ ክብረ ወሰን ስትናገር "እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ከማለት ውጪየምለው ነገር የለኝም" ብላለች።
ክርስቲና ባለፈው ታህሳስ በዋይትሰን ተይዞ የነበረውን የ289 ቀናት የህዋ ቆይታን ለማሻሻል ችላለች።
ይህም ክብረ ወሰን በቀጣይ በሚደረጉ የህዋ ጉዞዎች ሊሻሻል እንደሚችል አመልካች ነው ተብሏል።
ነገር ግን ዋይትሰን በተለያዩ ጊዜያት ህዋ ላይ በተደረጉ ቆይታዎች ብዛት ክብረ ወሰኑን እንደያዘች ስትሆን፤ በሦስት የተለያዩ ጉዞዎች ለረጅም ጊዜ ቆይታለች።
ክርስቲና ኮች በህዋ ላይ በነበራት ቆይታ 5,248 ጊዜ መሬትን የዞረች ሲሆን የ223 ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮች ጉዞን አድርጋለች።
ይህም ከመሬት ወደ ጨረቃ የሚደረግ የደርሶ መልስ ጉዞን ይሆናል።