ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተታለው ልቅ የወሲብ ምስላቸው የተሰራጨባቸው ሴቶች ካሳ ተፈረደላቸው
የአሜሪካው ፍርድ ቤት ተታለው ልቅ የወሲብ ተንቀሳቃሽ ምስላቸው በልቅ የወሲብ ድረ-ገጾች ላይ የተራጨባቸው 22 ሴቶች ካሳ እንዲከፈላቸው በየነ።
እድሜያቸው ከ18-23 የሆኑት 22 ሴቶች ልቅ ወሲብ እየፈጸሙ ለመቀረጽ የተስማሙት፤ ምስሎቹ በድረ-ገጾች ላይ እንደማይወጣ ተስማምተው ቢሆንም 'ገርልስዱፖርን' [GirlsDoPorn] በተሰኘ ድረ-ገጽ እና በሌሎች ላይ ተሰራጭቷል።
ለዚህም በጠቅላላው ለ22ቱ ሴቶች የ12.8 ሚሊዮን ዶላር (384 ሚሊዮን ብር በላይ) ካሳ እንዲከፈላቸው ተበይኗል።
የፍርድ ቤቱ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ወጣቶቹ በክፍያ ቪዲዮን ለመቀረጽ የተስማሙት፤ ምስላቸው ለግለሰቦች ለግል ስብሰብ ግብዓት ብቻ እንደሚሆን ከተናገራቸው በኋላ ነው።
የሳን ዲያጎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ 'የገርልስዱፖርን' ሥራ አስኪያጅን ቪዲዮቹን ከድረ-ገጹ እና ከሌሎች ገጾች ላይ እንዲያነሳ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
'ገርልስዱፖርን' በተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ የሚታዩት ሴቶች፤ የወሲብ ፊልም ተዋናይ ሳይሆኑ ገንዘብ ያጠራቸው አንድ ግዜ ብቻ የወሲብ ቪዲዮ የተቀረጹ ወጣት ሴቶችን እንደሚያቀርብ የክስ መዝገቡ ላይ ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ እንዳለው፤ ድረ-ገጹ ሴቶቹ ምስላቸው በድረ-ገጾች ላይ እንደማይጫኑ፤ ትክክለኛ ስማቸውንም እንደማይጠቀም እንዲሁም የሚያውቋቸው ሰዎችም ምስሎቹን እንማይመለከቱ ቃል ገብቶላቸው ነበር።
ፍርድ ቤቱ ግን የሴቶቹ ተንቀሳቃሽ ምስል ድረ-ገጹ ላይ ከመዋሉም ባሻገር፤ ወጣቶቹ ሊለዩባቸው የሚችሉበት የግል መረጃ ይፋ አድርጓል። በዚህም ከሴቶቹ አልፎ የቤተሰብ አባላቶቻቸው በኢንተርኔት ላይ የተለያየ መልክ ያላቸው የመብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ፍርድ ቤቱ አረጋግጫለሁ ብሏል።
የከሳሾቹ ጠበቃ፤ ደንበኞቹ ላይ የተለያየ አይነት ጥቃት ከመድረሱም ባሻገር፤ ለሞራል እና ለሥነ ልቦና ችግር ተዳርገዋል። ከሥራቸው የተሰናበቱ እና ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ጭምር እንዳሉ ገልጿል።
የ'ገርልስዱፖርን' ድረ-ገጽ ባለቤቶች ይግባኝ ማለት ከፈለጉ የ15 ቀናት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።