በባግዳድ የአሜሪካ ኤምባሲ በተቃዋሚዎች ጥቃት ደረሰበት

ባለፈው እሁድ አሜሪካ በኢራንና ኢራቅ ድንበር ላይ ካደረሰችው የአየር ጥቃት ጋር ተያይዞ በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በተቆጡ የአገሬው ተቃዋሚዎች ጥቃት ደርሶበታል።

በምላሹ የአሜሪካ ወታደሮች ወደግቢው ለመግባት የሚሞክሩ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተጠቀሙ ሲሆን አካባቢው ከባድ ውጥረት ነግሶበታል ተብሏል።

ለግቢው ጠባቂዎች የተሠራ አንድ ማማ በተቃዋሚዎቹ በእሳት መቀጠሉም ታውቋል።

ባለፈው እሁድ የአሜሪካ ወታደሮች ከካታይብ ሄዝቦላህ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የጦር ካምፖችን በአውሮፕላን ከደበደቡ በኋላ በትንሹ 25 ተዋጊዎች ሞተዋል።

አሜሪካ ካታይብ ሄዝቦላህ የተባለው ቡድን በአንድ የኢራቅ ኪርኩክ ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ባለፈው አርብ ባደረሰው ጥቃት አንድ ወታደሬ ተገድሎብኛል ብላለች።

የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አደል አብዱል ማህዲ ''አሜሪካ የፈጸመችው የአየር ጥቃት የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚጥስና ከአሜሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት እንድንመረምረው ያስገድደናል'' ብለዋል።

የካታይብ ሄዝቦላህ አዛዥ አቡ ማህዲ አል ሙሃንዲስ በበኩሉ ቡድኑ በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ኢራቅ የአሜሪካን እርምጃ ''ጥርት ያለ የሽብር ምሳሌ'' ነው ብላለች።

የዛሬው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በአሜሪካው የአየር ጥቃት የሞቱ የቡድኑ አባላት የቀብር ስነ ሥርዓት በሚደረግበት ወቅት ነው።

ከፍተኛ ወታደራዊና የሚሊሻ ኃላፊዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሀዘንተኞች 'አረንጓዴው ክልል' ወደሚባለውና በርካታ ኢራቅ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች ወደሚገኙበት ቦታ አቅንተዋል።

ኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞቹ ወደ ክልሉ እንዲገቡ ሲፈቅዱላቸው በቀጥታ ያመሩትም ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ነበር።

ተቃዋሚዎቹ የካታይብ ሄዝቦላህ እና ሌሎች የሚሊሻ ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ የተስተዋለ ሲሆን አሜሪካ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰነዘር ነበር። በርካቶችም በዋናው በር ላይ ድንጋይ በመወርወር፣ የቪዲዮ ካሜራዎችን በመስበርና ለጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ማማዎችን በማጥቃት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

በመቀጠልም ሰልፈኞቹ ከዋናው በሮቹ መካከል አንደኛውን ሰብረው መግባት ችለዋል።

አሶሺየትድ ፕረስ እንደዘገበው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በሩን ሰብረው አምስት ሜትር ያህል እንደተጓዙ የአሜሪካ ወታደሮች በአስለቃሽ ጭስ በመታገዝ እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል።

ሁኔታው ሲከሰት በኤምባሲው ውስጥ ምን ያህል ሠራተኞች እንደነበሩ የታወቀ ነገር የለም። ማረጋገጥ ባይቻልም አምባሳደሩ ቀደም ብለው እንዲሸሹ ተደርገዋል የሚሉ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።