ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ቴክሳስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ በተከፈተ ተኩስ ሁለት ሰዎች ተገደሉ
አንድ ታጣቂ በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ቤተ ክርስትያን ውስጥ በከፈተው ተኩስ ሁለት ሰዎች በፅኑ ካቆሰለ በኋላ በአንድ የታጠቀ የፀሎት ስነ ሥርዓት ታዳሚ ተገድሏል።
ታጣቂው ዌስት ፍሪዌይ ቸርች ኦፍ ክራይስት በተባለ ቤተ ክርስትያን ጥቃቱን ለመፈጸም 6 ሴኮንዶች የወሰዱበት ሲሆን ሰውየው ለምን ሲል ይህንን እንዳደረገው የታወቀ ነገር የለም።
የዋይት ሴትልመንት የፖሊስ ኃላፊ ጂፒ በቨሪንግ ታጣቂውን የተከላከሉት የቤተ ክርስትያኑ አባላትን ሥራ "የጀግና ድርጊት" ሲሉ አሞካሽተውታል።
ትላንት እሁድ ረፋድ ተኩሱ ሲፈፀም የጥዋት የፀሎት መርሃ ግብሩ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ ነበር።
በምስሉ ላይም ታጣቂው የቤተ ክርስትያኑ ጥግ ላይ ቆሞ አንድ የፀሎት ታዳሚን ሲያናግር ታዳሚውም እጁን ሲያወናጭፍ ታጣቂው ወደሱ መተኮስ ሲጀመር ያሳያል። ወድያውኑም ከአማኞቹ መካከል አንድ ሰው በተኩስ አፀፋውን መልሶ ታጣቂውን ሲጥል ያሳያል።
ምንም እንኳ የጠራ ምስል ባይገኝም ሌሎች የፀሎት ስነ ሥርዓቱን የታደሙ ሰዎችም ተኩሰዋል።
ፖሊስ እንዳለው ሁለቱ የቆሰሉት ሰዎች ሆሰፒታል እንደደረሱ ሕይወታቸው አልፏል። ባለስልጣኖች የሞቱትና የተገደለውን ታጣቂ ስም ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል።
የቴክሳስ አሰተዳዳሪ ግሬግ አቦት በበኩላቸው ጥቃቱን "ሰይጣናዊ ድርጊት" በማለት ከገለጹት በኋላ "የእምነት ቦታዎች የተባረኩ ናቸው፤ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስ የቤተ ክርስትያኑ አባላት ወድያውኑ የወሰዱት እርምጃ እጅግ ተገቢ ነው" ብለዋል።
የቤተ ክርስትያኑ ዋና አገልጋይ ጃክ ካሚንግስ ለኒውዮርክ ታይምስ እንዳሉት የታጣቂው አኳሃን የሚያጠራጥር ስለነበር የቤተ ክርስትያኑን የጥበቃ ቡድን ትኩረት የሳበ ነበር።
''የጥበቃ ቡድኑ አባላት በቤተ ክርስትያኑ መሣርያ ለመያዝ የተፈቀደላቸውና በፍቃደኝነት የሚያገለግሉ ናቸው ዛሬ የብዙ ሰው ሕይወት አድነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ሁኔታው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ይሆን ነበር" ብለዋል።
በቴክሳስ ግዛት ባለፈው ነሃሴ በተፈፀመ ጥቃት 22 ሰዎች ሲሞቱ 24 ሰዎች ደሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።