ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታላቋ ፀሐፊ ቶኒ ሞሪሰን ስትታወስ
የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋና ታዋቂዋ ፀሐፊ ቶኒ ሞሪሰን በ88 አመቷ ከዚህ አለም በሞት የተለየችው በትናንትናው ዕለት ነው።
የፀሐፊዋ ቤተሰቦች በጥልቅ ሐዘን ከአጭር ጊዜ ህመም በኋላ ማረፏን አረጋግጠዋል።
የአስራ አንድ መፃህፍት ደራሲዋ ቶኒ ሞሪሰን የኖቤል ሽልማትን ያገኘችው በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1993 ሲሆን የመጀመሪያ መፅሀፏን የፃፈችውም በ1970 ነው።
በጎርጎሳውያኑ 1987 የፃፈችው 'ቢላቭድ' ከአሳዳሪዎቿ ስላመለጠች ባሪያ ('ሴቴ')ና በልጇ ላይ የሚያጠነጥን ታሪክ ሲሆን በጎርጎሳውያኑ 1998 ወደ ፊልምም ተቀይሮ ኦፕራ ዊንፍሬይ ተውናበታለች።
ብዙዎች በተለይም በተለያዩ አለማት የሚገኙ ጥቁሮች ሀዘናቸውን ከመግለፅ በላይ ስራዋን እንዲሁም ለአራት አስርታት አመታት በፅሁፎቿ ፍቅርን፣ ነፃነትን፣ ማንነትን በተለየ መንገድ በመንገሯ ክብርን ለግሰዋታል፤ "ለሰጠሽንም ስጦታ እናመሰግናለን" የሚሉ መልዕክቶችንም አስተላልፈዋል።
ከሞቷ በላይ ስራዎቿን ከፍ ከፍ ልናደርግ ይገባልም ያሉ ብዙዎች ናቸው።
በአንድ ወቅት ፀሐፊዋ እንዲህ ብላ ነበር "እንሞታለን፤ ምናልባት የህይወት ትርጉሙ እሱ ይሆናል። ነገር ግን በቋንቋ ብዙ እንላለን። ምናልባት ህይወት የሚለካው በሱ ይሆናል"
የቶኒ ሞሪሰን ቤተሰቦች መግለጫ እንደሚያትተው "አፍቃሪዋ እናታችን፣ አያታችን እንዲሁም አክስታችን በትናንትናው ዕለት በቤተሰቦቿ ተከባ ህይወቷ አልፏል"።
ለቃላትም ሆነ ለፅሁፍ ልዩ ፍቅር የነበራት ቶኒ ሞሪሰን የራሷንም፣ የተማሪዎቿንም ሆነ የሌሎች ሰዎች ፅሁፍ የማንበብ ከፍተኛ ልምድ ነበራት።
"ምንም እንኳን መሞቷ ቢያሳዝነንም፤ ረዥም እና የተሳካና የተሟላ ኑሮ በመኖሯ ደስተኞች ነን" ይላል ከቤተሰቦቿ የወጣው መግለጫ
ቶኒ ሞሪሰን ኒውዮርክ በሚገኘው ሞንቲፊዮር የህክምና ማዕከል ነው ህይወቷ ያለፈው፤
መፅሀፎቿን ለረዥም ጊዜ በአርትኦት ስራ ሲሰራ የነበረው ሮበርት ጎትሊየብ በበኩሉ "በጣም ታላቅ ሴትና ታላቅ ፀሐፊ ነበረች፤ ከሁለቱ የትኛውንም ማስበለጥ እንደምችል አላውቅም" ብሏል።
የኖብ አሳታሚ ሊቀመንበር ሶኒ መህታ በበኩሏ " ከሰብዓዊነትና ለቋንቋ ጥልቅ ፍቅር ካላቸው ፀሀፊዎች አንዷ የሆነችው ቶኒ ሞሪሰን አይነት ፀሀፊዎች በቁጥር በጣም ጥቂት ናቸው"
የፃፈቻቸው ልብወለድ ስራዎችና በብዙዎች ዘንድ የሚዘከሩት 'ዘ ብሉየስት አይ'፣ ሱላ፣ ሶንግ ኦፍ ሰለሞን ፣ ታር ቤቢ፣ ቢላቭድ፣ ጃዝ፣ ፓራዳይዝ፣ ላቭ፣ ኤ መርሲ፣ ሆም፣ ጋድ ኸልፕ ዘ ቻይልድ፣ ይጠቀሳሉ።
ከኖቤል ሽልማት በተጨማሪ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1996 በአሜሪካ ስነ ፅሁፍ ላደረገችው አስተዋፅኦ የናሺናል ቡክ ፋውንዴሽን ሽልማትን ተቀብላለች።
እንዲሁም በ2012 ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የፕሬዚዳንቱ የነፃነት ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።
ቶኒ ሞሪሰን ራንደም ሀውስ በሚባለው ማተሚያ ቤትም በአርታኢነትና በአዘጋጅነት በማገልገል የመጀመሪያ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ሴት ናት።
ቦታ ለተነፈጋቸው ጥቁር ፀሀፍትም እድል በመስጠት የጌይል ጆንስ፣ ሄንሪዱማስ፣ መሀመድ አሊና የነፃነት ታጋይዋ አንጄላ ዴቪስ ስራዎችን ካሳተመቻቸው ጥቂት ስራዎች የተወሰኑት ናቸው።
ቶኒ ሞሪሰን በፕሪንስተን ዩኒቨርስቲም መምህር ነበረች።
በተለየ የታሪክ አነጋገር ዘይቤ ከፍተኛ ስፍራን ማግኘት የቻለችው ቶኒ በፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ አብራት የሰራችው ፕሮፌሰር ኖሊዌ ሩክስ እንደምትናገረው በመፅሀፎቿ ብዙዎች ያልደፈሩትን አከናውናለች ትላለች።
የመጀመሪያ መፅሀፏ ላይ ዋና ገፀ ባህርይ ሆና የተሳለችው ታዳጊ ጥቁር ናት፤ "ይህንን ጭቆና በተሞላባት አሜሪካ በተለይም በ1970ዎቹ ማን ያስበዋል" ትላለች።
"ብሉየስት አይ መፅሀፍ ሲታተም፤ የጥቁርን ማህበረሰብ ማእከል አድርጎ የሚፅፍ ማን ነበር? ማሰብ ያዳግታል። ማንም እንደሷ የፃፈ አልነበረም፤ እውነታውን ከአስጠሊታው ጋር አቆራኝታ፤ እንዲሁም አባጣ ጎርባጠውንም ሆነ መልካምነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ የፃፈ ብዙ የለም። " በማለት ምስክርነቷን ትናገራለች።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ብዙዎች ስራዋን በመጥቀስ ኃዘናቸውን እንዲሁም ለስነ ፅሁፉ አለም ያበረከተችውን አስተዋፅኦ በመዘከር ላይ ናቸው።
"የሃገሪቱ ሃብት ናት፤ በታሪክ ነጋሪነቷ ብቻ ሳይሆን ታላቅም ሰው ናት። ፅሁፎቿ ውበትን የተላበሱ ብቻ ሳይሆን የሞራል እሳቤያችንን እንዲሁም ህሊናችንን እንድንፈትሽ አድርጎናል። ከሷ ጋር ተመሳሳይ አየር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን መተንፈስ ስጦታ ነው" በማለት ባራክ ኦባማ ተናግረዋል።
"በዓለም ላይ እንደሷ ያሉ ሰዎች ያስፈልጉናል" ያሉት ደግሞ የስኮትላንድ ፖለቲከኛና መሪ ኒኮና ስተርጂዮን ናቸው።
ታዋቂዋ የቴሌቪዥን ፀሐፊ እንዲሁም አዘጋጅ ሮንዳ ራይምስ ስታድግ እሷን የመሆን ህልም እንደነበራት ገልፃለች።
"በጣም ማንበብ የምትፈልጉት ፅሁፍ ካለና እስካሁን ካልተፃፈ፤ ልትፅፉት ይገባል" በሚለው አባባሏም አስታውሳታለች።