ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴክሳስ የሚገኝ መገበያያ ውስጥ በተከሰተ ጅምላ ጥቃት 20 ሰዎች ሞተዋል
በአሜሪካዋ ቴክሳስ ክፍለ-ግዛት ውስጥ በምትገኝ አል-ፓሶ በተባለች ሥፍራ በደረሰ ጅምላ ግድያ 20 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 26 ደግሞ በፅኑ መጎዳታቸው ታውቋል።
የቴክሳስ ሃገረ-ገዥ ግሬግ አቦት ግድያው በግዛቲቱ ታሪክ አሰቃቂው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ዎልማርት የተባለ መገበያያ ሥፍራ ውስጥ ሃገር ሰላም ብለው ሲገበያዩ የነበሩ ሰዎች ናቸው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት።
ከግድያው ጋር በተያያዘ ፓትሪክ ክሩሲየስ የተባለ አንድ የ21 ዓመት ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አሳውቋል። ግለሰቡ ጥቃቱ ከደረሰበት አንድ ሺህ ኪሎሜትር ርቃ የምትገኘው የዳላስ ግዛት ነዋሪ ነው ተብሏል።
የሲሲቲቪ ካሜራው እንደሚያሳየው ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ጥቁር ቲሸርት አድርገው፤ በድምፅ መከላከያ መሰል ነገር ጆሯቸው ጀቡነው ነው ወደ መገበያያው የገቡት።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቱን 'የአረመኔነት መገለጫ' ሲሉ ገልፀውታል። በትዊተር ገፃቸው መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝደንቱ ጥቃት አድራሾቹን ያደረጉት ድርጊት ምንም ዓይነት ፍትሃዊ አመክንዮ የሌለው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
አሜሪካን ከሜክሲኮ ከሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በደረሰው በዚህ ጥቃት የሞቱ ግለሰቦች ስም እስካሁን ይፋ አልሆነም። የሜክሲኮው ፕሬዝደንት ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶር ግን ሶስት የሃገሬ ሰዎች ሞተዋል ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ጥቃቱ በሃገሪቱ አቆጣጠር ከረፋዱ 4 ሰዓት ሲሆን የደረሰው በርካቶች በድንጋጤ ሕንፃውን እየለቀቁ ሰወጡ ታይተዋል።
ካሊፎርኒያ ውስጥ በነበረ የምግብ ፌስቲቫል ላይ አንድ በአሥራዎቹ የሚገኝ አፍላ ሶስት ሰዎች ከገደለ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ነው ይህኛው የጅምላ ጥቃት የደረሰው።