በኢራቅ ጎዳናዎች ከፍ ያሉት ሴቶች

ከጥቅምት ጀምሮ ኢራቅ መንግሥትን በሚቃወሙ ለውጥ ፈላጊዎች እየተናጠች ነው። ተቃዋሚዎቹ የተለያዩ የማህበረሰቡን ክፍል የሚወክሉ ቢሆንም፤ አባታዊ ስርአት በከፍተኛ ሁኔታ በሰፈነባት ኢራቅ ሴቶች ተቃውሞውን ሲመሩት ተስተውሏል።

ያላቸውን አስተዋፅኦ ለማሳየት በመዲናዋ ባግዳድም የስዕል ስራዎች ተሰቅሎላቸዋል።

የዓመፁ ማዕከል የሆነው የባግዳድ ታህሪር አደባባይም ፈጠራ በተሞላባቸው ስዕሎች ተሞልቷል።

በተቃውሞቹ ላይ ከፍተኛ ስፍራ የነበራቸውን የኢራቅ ሴቶችን ጥንካሬና አይበገሬ መንፈሳቸውንም የሚወክሉ ስዕሎችም ተንፀባርቀዋል።

ብዚዎቹ የጥበብ ስራዎች የተሰሩት በሴቶች ሲሆን፤ በሃገሪቱ ውስጥ ሴቶች ሊኖራቸው የሚችለውን ሚናም ጠቋሚ ነው ተብሏል።

ተቃውሞዎቹም ሆነ እነዚህ የጥበብ ስራዎች የኢራቅ ሴቶች አንድ ላይ ተሰባስበው እንዲመጡ፣ በሃገራቸው ላይ ያላቸውን ቦታ እንደገና እንዲያጤኑትና ታሪክንም እንደገና እንዲፅፉ ማስቻሉም እየተነገረ ነው።

ምንም እንኳን ብዙ ሴቶች ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከባሎቻቸው ጫና ቢደርስባቸውም ይህንን በመቋቋም ተቃውሟቸውን አደባባይ ይዘውት ወጥተዋል። እስካሁንም ባለው አራት መቶ የሚሆኑ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል።

በብዙ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ዘንድ ችላ ተብለው የነበሩት ሴቶች የራሳቸውንም አጀንዳ ለመቅረፅ ተቃውሞውን እየመሩ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችና ወንዶች አብረው በማይተጋገዙባቸው መድረኮች እንደነዚህ የተባበሩ እንቅስቃሴዎች ማየት ከፍተኛ ለውጥን የሚያመጣም ነው ተብሏል።