ደቡብ ሱዳንና የዓለም ሙቀት መጨመር ምን አገናኛቸው?

ተመራማሪዎች በከባቢ አየር ላይ የሚቴን (CH4) ልቀት እየጨመረ መምጣት ምክንያቱ ምንድን ነው እያሉ ሲመራመሩ ቆይተው በመጨረሻም መልሱን ከደቡብ ሱዳን መስክ አገኘነው ብለዋል።

በኢደንብራ ዩኒቨርስቲ መሪነት በተደረገው ምርምር ከፍተኛ መጠን ያለው የሚቴን ልቀት ከደቡብ ሱዳን ረግረጋማ ስፍራ እንደሚመነጭ ተደርሶበታል።

በሳተላይት የተወሰዱ ምስሎች እንደሚያሳዩት የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ከቪክቶሪያ ሐይቅና ሌሎች ገባሪዎች ውሃ የሚያገኝ ሰፊ ረግረጋማ ስፍራ አላት።

ይህ ደግሞ ይላሉ አጥኚዎቹ ከረግረጋማ ስፍራ የሚመነጨውን የሚቴን ልቀት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።

እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2016 ከምስራቅ አፍሪካ የተወሰደው መረጃ ሲታይ በልቀት መጠኑ ከአለም ላይ ሶስተኛ ደረጃን ይይዛል ሲሉ ተናግረዋል።

"ያገኘነውን ውጤት መሬት ላይ ሄዶ እውነታውን ለማረጋገጥ ወይንም ደግሞ የተሳሳተ ነው ለማለት አይቻልም፤ ነገር ግን ያለን መረጃ ከዚህ ጋር የሰመረ ነው" ብለዋል ፕሮፌሰር ፖል ፓልመር።

" የሱዳኑ ረግረጋማ ስፍራ እየሰፋ ስለመሄዱ ገለልተኛ መረጃ አለን፤ ይህንን ደግሞ ከአየር ላይ የተወሰደው መረጃም ያሳያል፤ የበለጠ አረንጓዴ እየሆነ ነው የሄደው [አካባቢው]" ብለዋል ለቢቢሲ።

ሚቴን እንደ ካርቦን ኦክሳይድ ሁሉ ከፍተኛ አቅም ያለው የግሪን ሀውስ ጋዝ ሲሆን በከባቢ አየር ላይ በከፍተኛ መጠን በመገኘት ለዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ይሆናል።

ሚቴን በከባቢ አየር ላይ ያለው መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው።

በአለማችን ላይ ለሚቴን ልቀት ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የግብርና ስራ እና የቅሪተ አካል ነዳጅ መጠቀም መሆኑ ቢጠቀስም ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

የኢደንብራ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች በአፍሪካ ረግረጋማና ውሃ ገብ ስፍራዎች የጃፓንን ሳተላይት በመጠቀም በሚመለከቱበት ወቅት ከደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የሚቴን ልቀት እንደሚመነጭ መገንዘባቸውን ይናገራሉ።

ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2014 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን አካባቢውም ሱድ እንደሚባል ተናግረዋል።

ይህ የኤደንብራ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ቡድን ግኝቱን በሳይንስ ጆርናል ላይ ያሳተመ ሲሆን የሱድ ረግረጋማ ስፍራ ለዓለማችን የሚቴን ልቀት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ሲል ደምድሟል።

ዶ/ር ሉንት "ሠፊ ቦታን የሚሸፍን ነው፤ ስለዚህ ከዚህ ስፍራ ከፍተኛ መጠን ያለው ሚቴን ቢመነጭ የሚደንቅ አይደለም፤ ሱድ 40ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ስፍራ ነው" ብለዋል ለቢቢሲ።