ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
#6 እሷ ማናት?: ለነፃነትም ለጥበብም ያልታከቱ እጆች
ንግስቲ ገብረመስቀል እባላለሁ። በኤርትራ የነጻነት ትግል ወቅት በበርሃ መምህርት ነበርኩኝ። ከነጻነት በኋላ በአንድ የመንግሥት ጽሕፈት ቤት በሰነዶች ምዝገባ [ዳታ ኢንትሪ] ባለሙያ ሆኜ ሰርቻለሁ።
የውስጥ ፍላጎቴ ግን ሌላ ነበር። የሸክላ ሥራዎችና እደ ጥበብን አብዝቼ እወድ ነበር። ይህ ስሜቴ እየገፋኝ ሲመጣም የመንግሥት ሥራን ትቼ ወደዚህ ገባሁ።
እኤአ በ2003፣ በኤርትራ የጥልፍ ሥራ የተነቃቃበት ጊዜ ነበር፤ እኔም አቡጀዲ ላይ መጥለፍ ጀመርኩኝ። በዛን ወቅት በርካታ የሴቶችና የወንዶች የባህል ልብስ ሠራሁኝ።
በፈርጥ ያጌጡ ጌጣጌጦችንም እሰራ ነበር። ልጆች ሆነን ለትግል ወደ በርሃ ከመውጣታችን በፊት ወላጆቻችን እንዲመርቁን በክር ሹራብ ሰርተን ሰጥተን ነበር የምንሄደው።
በርሃ ላይም ሴት ታጋዮችን የእጅ ሞያ እንዲለምዱ፣ እዛው ባገኘነው ቀጭን ስልክ ሳይቀር በተለይ ደግሞ ለታጋይ እናቶች ለልጆቻቸው ካልሲ እንዲሰሩ እናስተምር ነበር።
በዚህ መንገድ ያደገው ልምድ ለእኔም እንጀራ ሆኖኝ፤ አሥመራ ላይ ስሜን የተከልኩ ባለሙያ እንድሆን ረድቶኛል።
የትግል ጓዶቼና የሚያውቁኝ ሰዎች ሥራዬ እንዲታውቅልኝም ሆነ ገበያ እንዳገኝ ወደ የተለያዩ ሥፍራዎች ሲሄዱ ምርቶቼን ይዘው በመሄድ እየሸጡ ያግዙኝ ነበር።
2005 ጥቅምት ወር ግን አንድ ትልቅ ነገር በሕይወቴ ተከሰተ። ከሁሉም የኤርትራ ዞኖች የተሰባሰብን 10 ሴቶች በአንዲት ክላውዲያ ዛምቦኒ የተባለች ጣልያናዊ መምህርት በኩል የሸክላ ሥራ ሥልጠና አገኘን።
ለተከታታይ አስር ወራት ሥልጠና ከወሰድን በኋላ ተመልሼ እጄን አጣጥፌ መቀመጥ አልፈለግኩም። በአንድ ወር ውስጥ የሚያስፈልገኝን እቃ አሟልቼ ወደ ሥራ ገባሁ።
በ2007 ላይ የሸክላ ሥራዎቼን ይዤ አሥመራ ከተማ ላይ በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ላይ ለዕይታ አቀረብኩ። ያኔ ይዤው የወጣሁት ሥራ በሙሉ ተሸጠ።
ያ ቀን የእንጀራ በሬን፣ ለሥራ ያለኝን ዓይኔን የከፈተ ሆነ። ትልቁ ሸክላ ሽጬ ያገኘሁት ገንዘብ 3 ሺ ናቅፋ [በአሁኑ የምንዛሬ ዋጋ 6320 ብር] ነበር።
[ሳቅ] በወቅቱ ትልቋንና ውድ የነበረችው የሸክላ ሥራዬ በፈርጥና በኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ያጌጠች የአምፖል አቃፊ [ላምፕ] ነበረች። አልሸጥኳትም! ለፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በስጦታ አበረከትኳት።
'ጣቶቻችን የተለዩ ናቸው'
የሸክላ ሥራ በጭቃ የሚሠራ ስለሆነ ትክክለኛውን አፈር ማግኘትና መምረጥ ከባዱ ፈተና ነው።
ጭቃውን ለማቡካት የሚያስፈልገው ጉልበት ደግሞ ሌላው ጭንቅ ነው። በእኔ አቅም ብቻ የሚሆን ስላልሆነ፤ የሚያግዘኝ ሰው ያስፈልገኝ ነበር።
ይህ ሁሉ ከተለፋ፤ ሥራውን ሰርቶ ገበያው ሊወደው የሚችለው ቅርጽና መልክ መስጠቱ ላይ ሌላ ጉልበት ይጠይቃል። በዚህ መካከል የተሰራበት አፈር ትክክለኛ ካልነበረ ይሰነጠቃል። ያኔ የማነባውን እንባ በቃላት መግለጽ አልችልም።
እድለኛ ሆኜ ይሄኛውን ደረጃ ካለፍኩኝ፤ ሸክላውን በእሳት መጥበስ አለብኝ። 20 ሰው መያዝ የሚችል ጉድጓድ እቆፍራለሁ። ጉድጓዱ ላይ እሳት ለማቀጣጠል ውስጥ ገብቼ ነው የምሠራው። ዐይኔና አፍንጫዬ ያነባል፤ ፊቴ ከሰል ይለብሳል።
ሥራው በጣም ከባድ ነው። በተለይ የመጨረሻው ደረጃ! ሸክላው ከእሳት ወጥቶ እስካይ ድረስ ያለኝ ስሜት ምጥ የተያዘች እናት የምትሰቃየው ስቃይ ያክል ነው።
የሸክላ ሰራተኛ ትዕግስተኛና የሙያው አፍቃሪ መሆን አለበት። በፍቅር ስትሰራው ሌሊቱ ሁሉ ኩልል ያለ ንጋት ያክል ይሆናል።
የሥራዎቼን ውጤት ሳይ ሁሌም እደሰታለሁ። አልቆ ሳይ የምደሰተው ደስታ ከቃላት በላይ ነው።
በዚህ ሙያ ውስጥ 14 ዓመት ሆኖኛል። ለ12 ዓመታትም ሰርቼበታለሁ። ቀደም ብሎ ሰው ለዚህ ሙያ ክብር አልነበረውም፤ ሰዉ 'ደግሞ ለጭቃ ሥራ' እያለ ሲያጥላላው ነበር። አሁን ግን ብዙዎች ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት ሥራ እየሆነ ነው።
በእኔ ሥር 20 ወጣት ሴቶች ይገኛሉ። በየቀኑ በምንሠራው ሥራ ደስተኞች ነን።
ለይምሰል አይደለም፤ ሴቶች ጣቶቻችን የተለዩ ናቸው። በቤታችን ውስጥ የምንሰራው ምግብ፣ የምናሳድጋቸው ልጆች፣ የቤታችን አያያዝ ማንነታችን የምናይበት መስታወታችን ናቸው።
ቤትን ማስተዳደር ቀላል አይደለም። ከዚህም አልፎ በእነዛ ውብ ጣቶችዋ እደ ጥበብን የማትሰራ ሴት ልጅ አለች ካላችሁኝ ማመን ይከብደኛል።
ሁሉንም ሴቶች ችሎታችሁን በአግባቡ በመጠቀም ለገበያ አቅርቡት እላለሁ። አቅምና ሙያ እያላት ቤት ውስጥ የምትቀመጥ ሴት ካለች ለእኔ ስንፍና ነው።
ሴቶች ችሎታቸውና ጥበባቸውን አውጥተው ለመጠቀም ግን ሊበረታቱና ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል። አቅምና ችሎታን ይዞ መቀመጥ ግን ተቀባይነት የለውም።
ዓለም ላይ በተለያየ ሙያ ያለን ሴቶች ተቀራርበን ከሰራን ደግሞ ታሪካችን ይቀየራል።