ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ተወሰነ
የጥምቀት ክብረ በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ መወሰኑን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አስታወቀ።
ድርጅቱ በኮሎምቢያ-ቦጎታ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ እያካሄደ ባለው ስብሰባ ነው የጥምቀት ክብረ በዓል አከባበር በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)ሆኖ እንዲመዘገብ ውሳኔ ያስተላለፈው።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የጥምቀት ክብረ በዓል አከባበርን፣ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።
ኢትዮጵያ እስካሁን ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶቿን የመስቀል በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡
የገዳ ሥርዓት በ2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተደረገው የዩኔስኮ ጉባኤ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ውጪ የማይዳሰስ ቅርሳቸውን ካስመዘገቡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ማላዊ፣ ኒስማ በሚባለው ባህላዊ ምግቧ፤ ሞሪሸስ ሙዚቃ፣ ዳንኪራና ዝማሬን ባካተተው ‹‹ሰጋ ታምቡር›› በሚባለው ባህላዊ ሙዚቃዋ፤ አይቮሪኮስት ዛዑሊ በሚባለው የጉሮ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንኪራ ይገኙበታል።
ጥምቀት በወርኃ ጥር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሮ የሚውል ኃይማኖታዊ በዓል ነው።
የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 11 ተጀምሮ በማግስቱ ጥር 12 ቃና ዘገሊላም በድምቀት ይከበራል።
ጥምቀት በኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዲስ አበባና ጎንደር ይገኙበታል።