ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የፀረ ሽብር አዋጅ ታሳሪዎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች
በፀረ ሽብር አዋጅ ተከሰው እስር ቤት የነበሩና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ክሳቸው ተሽሮ ነጻ የወጡ 300 የሚደርሱ ግለሰቦች ተሰባስበው የአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች ማኅበር መስርተዋል። የቀድሞ እስረኞች የህክምና፣ የትምህርት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመቋቋሚያና ሌሎችም ሊሟሉልን ይገባሉ ያሏቸውን ካሳዎች ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ቢሮ ጥያቄ ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ዳሰማ ሶሪን አነጋግረናል።
የአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች የተመሰረተው በነማን ነው? ለምንስ?
2010 ዓ. ም. መጨረሻ አካባቢ አብዛኞቻችን ከእስር ስንፈታ ምንም የምንሰባሰብበበት ወይም በመንግሥት በኩል ምንም የተደረገልን ነገር አልነበረም። ከተለያየ ቦታ ሰብስበው አሰሩን፤ ከዓመታት በኋላ ውጡ ተብለን፣ ወጣን። ሜዳ ላይ ነበር የተበተነው። 2011 ዓ. ም. መስከረም አካባቢ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ፒያሳ አካባቢ መሰባሰብ ጀመርን።
በማዕከላዊ የተደረገብን በደል አለ። የተዘረፍነው ንብረት አለ። ሌሎችም የመብት ጥያቄዎች አሉን ብለን ተሰባሰብን። ብዙ መጠለያ የሌላቸው አሉ። እስር ቤት ለዓመታት የቆዩ ናቸው። ቤተሰቦቻቸው ተበትነዋል።
እነዚህን እንዴት ከመብት አኳያ መጠየቅ አለብን? ብለን የተለያዩ ጠበቆችን አነጋገርን። ጥያቄያችንን ይዘን ጠቅላይ ሚንስተር ቢሮ ሄድን። ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ያሉ ሰዎች ማመልከቻችንን ተቀበሉና አዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ ሂዱ አሉን።
ከንቲባ ቢሮ ለሦስት ወራት ጥያቄያችንን ያለማቋረጥ አቀረብን። መጨረሻ ላይ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጥር 26 ካፒታል ሆቴል ፕሮግራም ይዘውልን ጥያቄያችንን አቀረብን። ጥያቄያችንን ሙሉ በሙሉ ተቀብለው፤ ያቀረባችኋቸው ጥያቄዎች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግም፣ በሕገ መንግሥታችንም አግባብ ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ ጥያቄዎቻችሁ በአስቸኳይ ይመለሳሉ አሉን።
በናንተ በኩል ማድረግ ያለባችሁን አድርጉና አቅርቡልን የሚል ምላሽ ሰጡን። ከዛ እያንዳንዱ የፖለቲካ እስረኛ የት እንደታሰረ፣ መቼ እንደታሰረ፣ የተፈረደበትን ፍርድ፣ የደረሰበት በደል፣ የትምህርት መረጃውን እና የቤተሰብ ኃላፊ መሆኑን በ1215 ገጽ ጽፈን ለከንቲባው ቢሮ አስገባን።
ያነሳችኋቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
የመጀመሪያው ጥያቄ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በነበርንበት ጊዜ ተገደን የሰጠናቸው ቃሎች፣ አሻራ እና የተሰጠብን ፍርድ አለ። ይህ መንግሥት በወቅቱ ይቅርታ የጠየቀበትና "እኛ ነን ሽብርተኛ" ብሎ ያመነው በመሆኑ፤ ሙሉ በሙሉ አሻራችን እንዲሰረዝልን፣ ፍርዱ እንዲነሳልን ነው የጠየቅነው።
አንዳንድ ልጆች ሥራ ሲያመለክቱ አሻራቸው በመጥፎ ይገኛል። የተፈረደብን በሽብር በመሆኑ ሥራ ለመግባት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳልን ነው የጠየቅነው። በማዕከላዊ የተወሰደብን ንብረት እንዲመለስልን ነው።
ብዙ ንብረት ተወስዶብናል። በማዕከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦም ሆነ በሌሎች እሥር ቤቶች ውስጥ በደረሰብን ድብደባ አካላችን የጎደለ፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰብን ስላለን ህክምና የምናገኝበት መንገድ እንዲመቻችልን ነው ሌላው ጥያቄ።
ሦስተኛው ጥያቄያችን ደግሞ ትምህርትን የተመለከተ ነው። በዩኒቨርስቲና የተለያዩ ተቋሞች ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ እና ያላግባብ ያቋረጡ አሉ። ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀናል።
ሌላው መጠለያን የሚመለከት ነው። እስር ላይ የነበሩ የተለያዩ የቤት እድሎችን እንዳያገኙ ሆነዋል። ሌላው መቋቋሚያን በተመለከተ ነው። ተዘዋዋሪ ፈንድ የሚባል አለ። በእስር ላይ በነበርንበት ወቅት ቤተሰቦቻችን ተበትነዋል። አሁንም ምንም ሥራ የሌላቸው ሰዎች ስላሉ ለነሱ ከተዘዋዋሪ ፈንድ መቋቋሚያ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ነው የጠየቅነው።
ሌላው በ27 ዓመታት በኢሕአዴግ መንግሥት ሕይወታቸው ያለፈ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ አጽማቸው ተሰብስቦ አንድ ቦታ እንዲቀበርና የመታሰቢያ ሀውልት እንዲቆምላቸው ነው ጥያቄያችን።
የምታነሷቸው ጥያቄዎች ምን ያህል የሕግ አግባብነት አላቸው?
ጥር 26 ከንቲባው በሰበሰቡን ወቅት አራት ጠበቆች ከኛ ጋር ተገኝተው ነበር። ጠበቃ አዲስ መሐመድ፣ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እና ሌሎችም ተገኝተው ከሕግ አንጻር አስፈላጊውን [ትንታኔ] አቅርበዋል።
አብዛኞቹ የፖለቲካ እስረኞች ያ ነገር ሲፈጸምባቸው የነበረው፣ ሲጎዱ የነበሩት ተገደው ነው፤ ዓለም አቀፍ ሕጉም ያግዛቸዋል [ብለዋል]። ሕገ መንግሥቱ ላይም የእያንዳንዱ ዜጋ መብት እና የአካል ደህንነት የተከበረ ነው፤ [መንግሥትም] ግዴታ አለበት [ብለዋል]።
በመንግሥት ደረጃ ያሉ ሰዎች የሰውን አካል አጉድለው፣ የሰውን ንብረት ዘርፈው፣ ሰውን እንደ ዜጋ እንዳይኖር ከልክለውት፤ እነሱ በሕግ ሳይጠየቁና ይሄ ሰው ከተፈታ በኋላም ሕጋዊ ድጋፍ ወይም ሽፋን እንዳያገኝ ማድረግ አግባብ ባለመሆኑ [ምላሽ] ይገባቸዋል ብለዋል። ወደፊት በሕግም እንሄድበታለን። አሁንም አንዳንድ የሕግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ሲሆኑ በይፋ እንገልጻቸዋለን።
ጥያቄዎችችሁን ካቀረባችሁ በኋላ ምን ምላሽ አገኛችሁ?
ከሚገባው በላይ ነው የተመላለስነው። መጀመሪያ ላይ ያቀረብናቸው ሰነዶች ኮፒ ጠፍቷል ተባለ። እንደገና ሌላ አዘጋጅተን ነው የሄድነው። ቤት የሌላቸው ዝርዝር አቅርቡ ተብለን፤ አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪ መሆናቸውን፣ ቤት እንደሌላቸው ከሚኖሩበት አካባቢ አጽፈው ያመጧቸውን ደብዳቤዎች ኮፒ ሰጥተን፤ በድጋሚ ጠፋ ከተባለ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ነው ያስገባነው።
ሆን ተብሎ ጥያቄያችንን ላለመመለስ የሚደረግ ጥረት እንደነበረ ነው [የምረዳው]። ትምህርትና ህክምናን በተመለከተ ጽፈንላችኋል ኑና ደብዳቤ ውሰዱ ብለውን ነበር። ሰው ግን ምን በልቶ ይማራል? ምን እየሠራ ይማራል? ቢሳካም እንኳን [ደብዳቤውን ሲሰጡን] የትምህርት ሰዓቱ አልፏል።
አብዛኞቹ ተቋሞች የምዝገባ ጊዜያቸው ተጠናቋል። ትምህርትም ተጀምሯል። አምና በክረምት የጠየቅነውን ጥያቄ፤ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲንከባለል የነበረ ጥያቄ፤ አሁን ጥቅምት ላይ ነው ለህክምናና ትምህርት ጽፈንላችኋል ያሉት።
መቋቋሚያን በተመለከተ እያንዳንዱ የፖለቲካ እስረኛ በአምስት በአምስት ተደራጅተው፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፈው እንዲያመጡ ተደርጎ፤ ፕሮፖዛል ሠርተው ካቀረቡ በኋላ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ ላይ እንዲመራ ተደርጎ ነበር። ቢያንስ ቢያንስ ሥራ ሠርተው ሌሎች ችግሮቻቸው ቀስ እያሉ ይመለሳሉ ብለን እዚህ [ጉዳይ] ላይ አጣድፈናቸው ነበር። በኋላ ግን የጻፉልን ደብዳቤ አነስተኛ የሥራ እድል እና ፈጠራ እንዲሁም አዲስ ብድርና ተቋም በአግባቡ እንዳይረዱን የሚያደርግ ነበር።
ደብዳቤው እንዳንረዳ አድርጓል ያልከው ምን የሚል ይዘት ስላለው ነው?
ተዘዋዋሪ ፈንዱ የተፈቀደው እድሜያቸው ከ34 ዓመት በታች ለሆኑ ነው። ከንቲባው ያሉት፤ ምንም ይሁን ምንም በልዩ ትዕዛዝ፣ በልዩ ሁኔታ እንድትስተናገዱ ይደረጋል ነበር። በልዩ ሁኔታ የምንስተናገድ ከሆነ የእድሜ ገደቡ ለኛ ተነስቷል ማለት ነው።
እኛጋ እድሜው ከ21 እስከ 78 ዓመት የሚደርስ ሰው ነው ያለው። ደብዳቤውን ሲጽፉልን ግን ተባበሯቸው የሚል እንጂ የእድሜ ገደቡ መነሳቱን የሚመለከት ምንም ነገር አልጻፉልንም። ስንደራጅ ደግሞ ሁሉም በእድሜ ከሚመጥነው ጋር ስለሆነ የተደራጀው ለመምረጥ አስቸጋሪ ሆነ።
ደብዳቤው ከተበተነ በኋላ አስፈላጊውን ትብብር ያደረጉልን ሰዎች አሉ። አነስተኛና የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የሚገኙ ሰዎች፤ በአንድ ሳምንት 141 ሰው የተደራጀበትን ወደ 30 ምናምን ፕሮጀክት አጥንተው፣ የሚስተካከለውን አስተካክለው ወደ ታች እንዲወርድ አደረጉልን። ክፍለ ከተማ ስንሄድ፤ ታች ውረዱና በወረዳ ላይ ተደራጁ እንጂ እኛ አናደራጃችሁም ብለው መለሱን።
ከላይ ፕሮጀክቱ ተሠርቶ አልቆ፣ ፕሮጀክቱ ታርሞ፣ ተስተካክሎ ነው የመጣው፤ እንዴት ከታች እንደራጃለን? ስንል ምንም የምናውቀው ነገር የለም ብለው መለሱን። ደብዳቤያችን በዚህ ምክንያት ተቀባይነት አጣ። ከዛ ደብዳቤውን አስተካክሉልን ብለናቸው፤ ደብዳቤው ተስተካክሎ ሲሰጠን ደግሞ ለተዘዋዋሪ ፈንዱ የተመደበው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አልቆ ነው ያገኘነው።
አልቋልና ድጋሚ ገንዘብ እስኪመጣ ጠብቁ ነው የተባልነው። ለዓመታት በእስር ሲማቅቅ የነበሩ ሰው፣ ቤተሰቦቹ የተበተኑ፣ አካሉ የጎደለ ሰው ነው ያለው። ይህን ሰው ለመድዳት ዳተኛ ከመሆን የመነጨ እንጂ ፍላጎቱ ቢኖር ኖሮ የአንድ እና ሁለት ሳምንት ሥራ ነበር።
የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የጠየቃችሁትን እስካሁን ያገኘ አለ?
ማንም አገልግሎት ያገኘ ሰው የለም።
1215 ገጽ የሆነው ሰነድ የምን ያህል ሰዎች ኬዝ ነው?
300 ገደማ እንደርሳለን። እያንዳንዱ ሰው ባለ ትዳር መሆኑ እና አለመሆኑን ያረጋገጥንበት ሰነድ አለ። ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተፈረደበት ፍርድና መፈታቱን የሚገልጽ ደብዳቤ አለ።
ከወህኒ ቤት የተፈታበት ደብዳቤም አለ። የአዲስ አበባ ነዋሪ ለመሆኑ የቀበሌ መታወቂያው ኮፒ አለ። የአዲስ አበባ ነዋሪ ሆኖ በስሙ የተመዘገበ መጠለያ የሌለው (የኪራይ ቤቶች አስተዳደርም ሆነ የግል ቤት) መሆኑን፣ የትምህርት ደረጃውን፣ ከትምህርት መባረሩን እና ህክምና እንደሚያስፈልገው የሚገልጹ ሰነዶች ናቸው።
ለጠየቃችኋቸው ጥያቄዎች የተሰጧችሁ መልሶች ውጤታማ እንዳልሆኑ ማለትም፤ ተዘዋዋሪ ፈንዱ በእድሜ መገደቡ፣ የትምህርት መመዝገቢያ ጊዜ ማለፉ፣ የህክምና አገልግሎት አለማግኘታችሁንም ገልጻችሁ ዳግመኛ ጥያቄ አቅርባችኋል?
አቅርበናል። ተዘዋዋሪ ፈንዱን በተመለከተ ከንቲባው ጋር ቀርቧል ነው ያሉን። ከሁለት ወር በላይ ጠብቀናል። ምንም መልስ የለም። ከንቲባውን ለማግኘት ሦስት ጊዜ ጠይቀናል ምላሽ አላገኘንም። የሚነገረን ሌላ ነው። የሚሠራው ሌላ ነው።
ለጥያቄዎቻችሁ መልስ እንዳላገኛችሁና ወደ ቀጣዩ እርምጃ እንደምትሄዱ ተናግራችኋል ቀጣዩ እርምጃችሁ ምንድን ነው?
የመጀመሪያው እርምጃችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዩን እንዲያውቅልን ማድረግ ነው። ይህ ብቻም አይደለም። ለምሳሌ በእስር ሲማቅቁ ለነበሩ መቋቋሚያ የሚሆን ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተረዱ የተባሉ ገንዘቦች አሉ።
በአሀዝ ተጠቅሶ ያለው ገንዘብ ይታወቃል። የእነዚህን ማስረጃ እየሰበሰብን ነው። ክቡር ከንቲባው ማዕከላዊ ሄደው፣ ቀለም አስቀብተው፣ ለዓመታት ሰዎች ሲሰቃዩበት፣ አካል ሲጎድልበት የነበረውን ቦታ ሙዝየም እንዲሆን ክር በጥሰው ገብተዋል።
ጥሩ ነው። ማዕከላዊን ቀለም ከመቀባት ባለፈ እዛው ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች ግን አንድም ሰው ዞር ብሎ አላያቸውም። ሜዳ ላይ ተበትነው ነው የቀሩት። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ የፈለግነው ይህን ነው። የፖለቲካ ጨዋታ ነው የተያዘው። ከዚህ በፊት ትግል ስናደርግ የነበረው ካሳ እንድናገኝ የተለየ ጥቅም እንድናገኝ አይደለም።
ቢያንስ ያፈሰሱትን ደም ይጥረጉ፣ የሰበሩትን አጥንት ይጠግኑ፣ ያረገፉትን ጥርስ ይተኩ ነው ያልነው። ጥያቄያችን ሌላ አይደለም። ያደረሱብንን በደል፤ ከቃላት ባለፈ፤ በኛ ይብቃ የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያረጋግጥ የሆነ ነገር ያድርጉ ብለን ነው የጠየቅነው። ግን አንዱንም ለማድረግ ፍቃደኛ አይደሉም።
ለቀድሞ እስረኞች መቋቋሚያ የሚሆን የገንዘብ እርዳታ አለ ያልከውን ብታብራራልን?
እሱን እኛ ራሳችን እያጣራን ነው። ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲያውቁልን የፈለግናቸው ነገሮች አሉ። ሆነ ተብለው ተሸፍነው የተዘለሉ ነገሮች አሉ። እነሱን ጊዜው ሲደርስ እናወጣቸዋለን።
ለሕዝብ ከማሳወቅ ባለፈ ለጥያቄዎቻችሁ አሁንም መልስ ካላገኛችሁ ምን ታደርጋላችሁ?
ወደ ሕግ ከመሄዳችን በፊት ያቀድናቸው ነገሮች አሉ። ቤተሰቦቻችንን እና የተጎዱ ሰዎችን እና ደጋፊዎቻችንን ሰብስበን ሰላማዊ ሰልፍ የመጥራት እቅድ አለን። የረሀብ እድማና ሌላም ያቀድናቸው ነገሮች አሉ። ጊዜያቸው ሲደርስ እንገልጻቸዋለን።
አንተ የታሰርከው መቼ ነበር?
ፍሪላንስ ሆኜ የተለያዩ የግል ጋዜጣዎች ላይ እሠራ ነበር። አሁን በተፈረደብኝ ፍርድ የታሰርኩት 2007 ዓ. ም. ላይ ነበር። በጻፍኩትና በሬድዮ ላይ በሠራሁት ነገር ነበር የተከሰስኩት። ከተፈረደብኝ በኋላ እስከ 2010 ዓ. ም. ታስሬያለሁ። ግን ከዛ በፊትም በተደጋጋሚ በጋዜጠኝነት ሥራዬ ማዕከላዊና ሦስተኛ ወንጀል ምርመራም ታስሬያለሁ።