በኡጋንዳ 16 ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ሞቱ

በኡጋንዳ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዓለማቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ።

በሀገሪቱ ምዕራባዊ ቡንዲቡግዮ አካባቢ በጎርፍ ተወስደው ህይወታቸው ያለፉ ዜጎችን ሬሳ የመሰብሰብ ሥራ የተከናወነ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አሁንም ጎርፍ ሊያጋጥምባቸው በሚችሉ ስፍራዎች እየተንቀሳቀሱ ነው ብሏል ቀይ መስቀል።

ከዚህ በተጨማሪ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና ዋና ዋና መንገዶች በጎርፉ ምክንያት ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ለነዚህ ሁሉ ሚቲዎሮሎጂካል ክስተቶች ምክንያቱ የሕንድ ውቅያኖስ ነው ብለዋል ተመራማሪዎች።

በሶማሊያም ነፋስ በቀላቀለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ባጋጠመው አደጋ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን ኤይል የተባለችው ከተማን ከተቀሩት አካባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶችና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል ተብሏል።

በኡጋንዳ ባለፉት ሳምንታት ያለማቋረጥ ሲጥል የነበረው ዝናብ ባለፈው አርብና ቅዳሜ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ነው የጎርፍ አደጋው የተከሰተው።

ፖሊስ፣ የመከላከያ ሀይል፣ የእርዳታ ድርጅቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች በመተባበር በአደጋው የተጎዱትን የመርዳትና ሌሎች ሟቾችን የማፈላለግ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ታውቋል።

የጎርፍ አደጋው ባጋጠመባቸው አካባቢዎች ማንኛውም አይነት መገናኛ አማራጮች በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ ከባድ አድርጓል።

ይህንን ተከትሎም የኡጋንዳ አደጋ መከላከል ኤጀንሲ ዜጎች በእግራቸው መንቀሳቀስ፣ መኪና ማሽከርከር፣ ወንዞች አካባቢ መንቀሳቀስም ሆነ ጎርፎችን ለማቋረጥ እንዳይሞክሩ አስጠንቅቋል።

በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ታንዛኒያ እንዲሁም ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ያለማቋረጥ የጣለ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍና የመሬት መንሸራተት እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 300 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የተባበሩት መንግስታት ገልጿል።