በመቀሌ ከተማ ፆታዊ ጥቃትን በመቃወም ሊደረግ የነበረው ሰልፍ ተከለከለ

ባለፈው ሳምንት በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን፤ ሕዝብና የመንግሥት አመራሮች ግምገማ ካደረጉ በኋላ ሦስት ሴቶች በአንድ የፖሊስ አባል ጥቃት ተፈፅሞብናል ሲሉ ተናግረው ነበር።

የአዲ ዳዕሮ ከተማ ፖሊስ አባል የሆነው ተጠርጣሪ አንዲት ሴት በመድፈር ክስ የቀረበበት ሲሆን ሌሎች ሴቶችም በዚሁ የፖሊስ አባል ላይ ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልፀው ነበር። ተከሳሹ ጉዳዩ እስከሚጣራ በስድስት ሺህ ብር ዋስ መለቀቁ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ይህንን ተከትሎ ተጠርጣሪው የፖሊስ አባል አልታሰረም በሚል መስከረም 28 2012 ዓ.ም የከተማው ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ቁጣውን መግለፁ የሚታወስ ነው።

በጊዜው በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠን የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ መሆኑን በመግለፅ "ክስ ያቀረበችበት አንዲት ሴት ናት፤ የቀረበበት ክስም በሕጉ ዋስትና የሚያስከለክለው አይደለም" ብሏል።

በመሆኑም ግለሰቡ በዋስ ተለቆ ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ አስታውቆ ነበር።

ይህንኑ ተከትሎ በመጭው እሁድ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመቃወም በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በከተማ አስተዳደሩ መከልከሉ ተሰምቷል።

የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆነችው ዶ/ር ሄለን ቴዎድሮስ ስለ ክልከላው "ማድረግ ያለብንን ሂደት ነው የተከተልነው፤ እኛ ያገባናል ብለን የተሰበሰብን ልጆች ፊርማችን ያለበት እና ለሰልፉ ኃላፊነት እንደምንወስድ ደብዳቤ ፅፈን ወደሚመለከተው አካል፤ መቀሌ ከተማ አስተዳደር ነው የሄድነው።" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ዶ/ር ሄለን እንደምትለው ሄደው ባነጋገሯቸው ወቅት የመንግሥት አካል ካልሆነ በስተቀር በግለሰቦች ደረጃ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ እንደማይችል በመግለፅ እንደተከለከለ ነገረዋቸዋል።

"ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ነው የሚሄደው፤ አዲ ዳዕሮ የተፈጠረውን ነገር ማንሳት ይቻላል" የምትለው ዶ/ር ሄለን ምንም እንኳን ግለሰቡን የተመለከተ የተለያዩ ወሬዎች ቢወሩም፤ አንዲትም ሴት ትሁን 50 ሴቶች መደፈራቸውን ሄደው መናገራቸውን ታስታውሳለች።

"ተጠርጣሪው ግለሰብ በ6 ሺህ ብር ዋስ ተለቋል፤ ለዚያውም የሕግ አስከባሪ የሆነ ፖሊስ። ይህም ትልቅ ነገር ነው የሚያሳየን። የብዙ ሴቶችን ታሪክ እናውቃለን፤ ተጠርጣሪዎቹ በትንሽ ብር ዋስ ነው የሚለቀቁት፤ ስለዚህ መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት እየሰጠው አይደለም" ስትል ትወቅሳለች።

በዚህም ምክንያት ነበር ጉዳዩ ያገባናል የሚሉና ከተለያየ ሙያ የተውጣጡ ግለሰቦች ተሰባስበው ድርጊቱን በመቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተነሱት።

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የመቀሌ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማይ ተስፋይ፤ "ሰልፍ ለማካሄድ ጥያቄ ላቀረበ ሁሉ ማስተናገድ አይቻልም። ዓላማው መታወቅ አለበት" ብለዋል።

አቶ ግርማይ ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጥያቄ ላቀረቡት ግለሰቦች የሕጋዊ ድርጅት ማህተም ያለው የድጋፍ ደብዳቤ እንዲያመጡ ከመጠየቅ በዘለለ ሰልፍ ማካሄድ አልከለከልንም ሲሉ ግለሰቦቹ ያቀረቡት ደብዳቤ ማህተም እንደሌለው ገልፀዋል።

ኃላፊው አክለውም ሰልፉን ለማካሄድ የሲቪክ ማህበረሰብም ይሁን የመንግሥት ድጋፍ ያለው ደብዳቤ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።